የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ግንባታ የመሠረት ቁፋሮ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው የራሱ ግቢ ውስጥ የዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ቁፋሮ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

G+34 የሆነ ዘመናዊ ህንፃ ከሶስት የምድር በታች ወለሎች ጋር ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት የዋናው ህንፃና የአንዱ ክንፍ የአፈር ድጋፍ ሥራ ተጠናቆ የመሠረት እና የምድር በታች ወለሎች ቁፋሮ በተያዘለት መርሃ-ግብር እየተከናወነ መሆኑን ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡

የህንፃው የቁፋሮ ሥራ በሶስት ምዕራፎች ተከፍሎ እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን የመጀመሪያው ምዕራፍ መቆፈር ካለበት 15 ሜትር ውስጥ 4 ሜትር የቁፋሮ ሥራ ማከናወን ተችሏልም ተብሏል፡፡ ይህ የግንባታ ምዕራፍ  ዋናው የህንፃው G+34 ታዎር የሚቆምበት ቦታ በመሆኑም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ቢሮው አስታውቋል፡፡

ሁለተኛው የቁፋሮ ምዕራፍ መቆፈር ካለበት 15 ሜትር ውስጥ 8 ሜትር የቁፋሮ ሥራ ማካሔድ የተቻለ ሲሆን የሶስተኛው የቁፋሮ ምዕራፍ ግን ሁለቱ የምዕራፎች የቁፋሮ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደሚጀመር ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡

ከፕሮጀክቱ ግንባታ ጎን ለጎንም ህንፃው በሚገነባበት አካባቢ አቋርጦ የሚያልፈውን ባለ132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በመሬት ውስጥ ለመዘርጋት የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ነው ለማወቅ የተቻለው፡፡

ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ የህንፃ ግንባታውን በ2012 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 25 በመቶ በማከናወን አጠቃላይ አፈፃፀሙን 28 በመቶ ለማድረስ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ በላከው መረጃ ገልጿል፡፡

ይህ የተቋሙ ህንፃ ከምድር በታች የሚገነቡትን ወለሎች ጨምሮ በአጠቃላይ 47,881 ሜትር ስኩዌር የመሬት ሽፋን ላይ የሚያርፍ ይሆናል፡፡

የህንፃው ግንባታ አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪ 2 ነጥብ 4 ቢሊዬን ብር ሲሆን ወጪውም ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሆነ ታውቋል፡፡

የግንባታ ሥራውን የቻይናው ሲ.ጂ.ሲ.ኦ.ሲ (CGCOC) ኩባንያ እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ኤም.ኤች.ኢንጂነሪንግ ደግሞ በማማከር ሥራ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡

የህንፃው መገንባት ተቋሙ የተሰጠውን ሃገራዊ ተልዕኮና ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ከማገዙም ባሻገር አገልግሎት አሰጣጡን ፈጣንና ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝ ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

five + five =