የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጥቃት የተፈፀመበት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ተዘከረ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ አመራሮች እና ሠራተኞች ‹‹አልረሳውም! እኔም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ›› በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጥቃት የተፈፀመበትን አንደኛ ዓመት አስበዋል፡፡
በህዝብና በመንግሥት የተጣለባቸውን ግዳጅ ሲወጡ በጁንታው ኃይል ክህደት ለተሰው የመከላከያ ሠራዊት አባላትም የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ ዘክረዋል፡፡
በዋና መስሪያ ቤት በተካሔደው መርሃ-ግብር ላይ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አማካሪ አቶ አንዳርጌ እሸቴ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የጁንታው ቡድን የፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ እንኳን በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይቅርና በዓለም ህዝብ አዕምሮም የሚረሳ አይደለም ብለዋል፡፡
የሰሜን ዕዝ ሠራዊት አባላት በትግራይ ክልል የህዝቡን ሠላም ከመጠበቅ ባሻገር ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አዝመራ እያጨደና ከዕለት ጉርሱ በመቀነስ ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ እየገነባ የቆየ የሃገር አልኝታ እንደነበር አቶ አንዳርጌ አስታውሰዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሃገር የማፍረስ እኩይ ተልዕኮውን ለማስፈፀም ሲል ለበርካታ ንፁሃን ዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል ያሉት አማካሪው በቀቢፀ ተስፋ የተሞላው ዕቅዱ በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በክልል ልዩ ኃይሎች እና በአካባቢ ሚሊሻዎች እየከሸፈበት እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያውያን የጋራ ትግል ከሥልጣን የተወገደው የጁንታው ቡድን በጎንደር፣ በአፋር እና በወሎ አካባቢዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን በመፈፀም እንዲሁም ንብረቶችን በመዝረፍና በማውደም የሽብር ተልዕኮውን በአደባባይ አሳይቷል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የሠላማችን ዘብ በሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈፀመበትን አረመኔያዊና ፋሽሽታዊ ድርጊት በመቃወምና በማሰብ በቀጣይ ለሚደረጉ ልዩ ልዩ የሰው ኃይል፣ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና የሃሳብ ድጋፎች አመራሩ እና ሠራተኛው ዝግጁ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሁሉም ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙርን በመዘመር ለጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነት እና ክብር ገልፀዋል፡፡
0 Comments