የአዳማ ሁለት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያና ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡

Published by corporate communication on

የአዳማ ሁለት ባለ 230/132/15 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያና ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ አስታወቀ፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ሽኩር እንዳስታወቁት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እና የማስተላለፊያ መስመር ግንባታው 97 በመቶ አፈፃፀም ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ እየተገነባ ነው ያሉት አቶ መሐመድ በምዕራፍ አንድ በአዳማ ከተማ አዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እና በነባሩ የአዳማ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የካፓሲተር ባንክ ማስፋፊያ የዲዛይን፣ የአቅርቦት፣ የግንባታ፣ የፍተሻ እና የሙከራ ሥራዎችን ያጠቃልላል ተብሏል፡፡

በምዕራፍ ሁለት ደግሞ 1.7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ባለ 230 ኪሎ ቮልት ከነባሩ የቆቃ-ሁርሶ ወደ አዳማ ሁለት እና 3.8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ባለ 132 ኪሎ ቮልት ከነባሩ የአዳማ-መተሃራ ወደ አዳማ ሁለት ጥምር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የግንባታ፣ የፍተሻ እና የሙከራ ሥራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ የአዳማ ሁለት ባለ 230/132/15 ኪሎ ቮልት አዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ እና የፍተሻ ስራ ተጠናቆ አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

3.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ባለ 132 ኪሎ ቮልት ከነባሩ የአዳማ-መተሃራ ወደ አዳማ ሁለት ጥምር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ተጠናቆ ለፍተሻ ስራ ዝግጁ መደረጉንም ነው ኃላፊው የገለፁት፡፡

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ 15 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ያሉት እንደሆነም ጨምረው አብራርተዋል፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያውን ሲዩአን ኤሌክትሪክ (Sieyuan Co., Ltd.) የተባለ የቻይና ኩባንያ እየገነባ የሚገኝ ሲሆን ከነባሩ የአዳማ-መተሃራ እስከ አዳማ ሁለት ጥምር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ያለው ግንባታ ደግሞ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሲቪል ኮንስትራክሽን ቢሮ በኩል እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡

 የማማከር ሥራውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኢንጅነሪንግ ቢሮ እየሰራ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የፕሮጀክቱ መገንባት የአዳማ ከተማን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ለመመለስና በአካባቢው ለተገነባው የኢንደስትሪ ዞን ኃይል ለማቅረብ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

 

 

 

 

 

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

eight + ten =