የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ስድስት ተርባይኖች ተከላ ተጠናቀቀ

Published by corporate communication on

የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ስድስት ተርባይኖች ተከላ ተጠናቆ የሙከራ ኃይል ለማመንጨት ዝግጁ መሆናቸውን የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ቀለሙ ገለፁ፡፡

ለሙከራ ለሚያስፈልጉ ተርባይኖች፤ የውስጥ ገመድ ዝርጋታ ስራ በመከናወን ላይ መሆኑንም አቶ ታረቀኝ አስታውቀዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ እንደገለፁት የሙከራ ሥራውን ለማከናወን የማከፋፈያ ጣቢያዎች ሥራና ከብሔራዊ የኃይል ቋት ጋር የማገናኘት ሥራ መጠናቀቅ እንደሚኖርበት ገልፀዋል፡፡

ስለሆነም የሙከራ ሥራውን ለማከናወን በአሁኑ ሰዓት ቀሪ የማከፋፈያ ጣቢያ፣ የማስተላለፊያ መስመሮች፣ የታወር ተከላና ገመድ ዝርጋታ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቶት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ነው  አቶ ታረቀኝ ያብራሩት፡፡

በኃይል ማመንጫው እያንዳንዳቸው 2 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ 48 ተርባይኖች የሚኖሩት ፕሮጀክቱ፤ የ34 ተርባይኖች ታወር የመሰረት ግንባታ ኮንክሪት ስራ ተከናውኗል፡፡

የቀሪ ተርባይኖች የታወር እና የቦክስ ትራንስፎርመር መሰረት ግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡

በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ፕሮጀክቱ ፕሮጀክቱ በሚገነባበት ቦታ የከርሰ ምድር ውሃ ተቆፍሮ አለመገኘቱ፣ ባለፈው ክረምት በነበረው ከባድ ዝናብና ጎርፍ ምክንያት ስራው ተስተጓጉሎ መቆየቱና በደለል የተደፈኑ ጉድጓዶችን እንደገና ለመስራት መገደዱ እንዲሁም ኮንትራክተሩ ለሰራው ስራ የጠየቀውን ክፍያ አበዳሪው ባንክ በወቅቱ አለመክፈሉ በግንባታ ሂደቱ ላይ ተጽዕኖ  መፍጠሩን አቶ ታረቀኝ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓትም የመርሃ ግብር ክለሳ በመሰራት ላይ ሲሆን የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 46 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል፡፡

ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ በ700 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሱማሌ ክልል አይሻ ደወሌ ወረዳ በመገንባት ላይ የሚገኝ ሲሆን ለግንባታውም 15 በመቶው በኢትዮጵያ መንግስት ቀሪው 85 በመቶ ደግሞ በቻይና ኤግዚም ባንክ የሚሸፈን 257 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደተመደበለት ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

twelve + 10 =