የአዘዞ – ጭልጋ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ እየተፋጠነ ነው

Published by corporate communication on

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ማዕከላዊ ጎንደር ዞን እየተገነባ የሚገኘው የአዘዞ – ጭልጋ ባለ 230/33 ኪ. ቮ. የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ አንድ አዲስ ባለ 230/33 ኪ. ቮ. ከፍተኛ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እና 40 ኪ ሜ. ርዝመት ያለው የባለ 230 ኪ. ቮ. የኃይል መስመር ዝርጋታን ያጠቃልላል፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያው የሳይት ተቆጣጣሪ መሃንዲስ አቶ አድማሱ ኃይሌ እንደገለፁት የጭልጋ ባለ 230/33 ኪ.ቮ. ማከፋፈያ ጣቢያ የተለያዩ የሲቪል እና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ከሐምሌ 2011 ዓ.ም. እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

እንደ አቶ አድማሱ ገለጻ በማከፋፈያ ጣቢያው እስከ አሁን የኤሌክትሮ መካኒካልና የብረታ ብረት ተከላና ለኤሌክትሪክ ገመዶች ቀበራ የሚውል ግንባታ ስራዎች ተጠናቀዋል፡፡

የመቆጣጠሪያ ቤት፣ የሰራተኞች መኖሪያ ቤት፣ የጥበቃ ቤት ግንባታና የፍሳሽ ማስወገጃ ግንባታዎች የማጠናቀቂያ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በቀጣይም የጠጠር ንጣፍ፣ የውስጥ አጥር፣ የሲዊችያርድ ግንባታ እና የሁለት ባለ 31 ነጥብ 5 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር ተከላ ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚከናወኑ መሃንዲሱ ጠቁመዋል፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያው አጠቃላይ አፈጻጸም 63 በመቶ ደርሷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከነባሩ የአዘዞ ባለ 230/66/33/15 ኪ ቮ. የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተነስቶ አዲስ እስከሚገነባው የጭልጋ ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ የሚዘረጋው የ40 ኪ.ሜ ባለ 230 ኪ. ቮ. ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታም እየተፋጠነ ነው፡፡

የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታው የሳይት ተቆጣጣሪ መሃንዲስ አቶ ሃብታሙ ኃይሉ እንደተናገሩት ለመስመር ዝርጋታው 105 ማማዎች ይተተከላሉ፡፡

ከዚህ ውስጥ ደግሞ የ22 ምሶሶ መትከያ የመሰረት ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን 50 የምሶሶ ማቆሚያ የጉድጓድ ቁፋሮ ስራም እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ግንቦት 2012 ዓ.ም. የተጀመረው የመስመር ዝርጋታ ስራው አጠቃላይ አፈጻጸም 10 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡

የአዘዞ – ጭልጋ – ፊንጫ 2ኛ – ሻምፑ – መቱ – ማሻ 230/33 ኪ.ቮ. ፕሮጀክት ዋና ማናጀር አቶ ግርማ ዘለቀ እንደተናገሩት የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታውን እና የመስመር ዝርጋታ ስራውን ለማጠናቀቅ ከ281 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ተመድቦለታል፡፡

ፋይናንሱም ሙሉ ለሙሉ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የሚሸፈን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሥራውን ለመጨርስ 18 ወራት የተያዘለት ሲሆን ግንባታውን ሲኖ ሃይድሮ ኮርፖሬሽን የተባለው የቻይና ኩባኒያ ሲያከናውን በአማካሪነት ደግሞ ኢ. ኤል. ሲ. ELC የተባለ የጣሊያን ኩባኒያ እየተሳተፉበት ይገኛሉ፡፡

ስድስት ባለ 33 ኪ. ቮ. ወጪ መስመር ያሉት ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በጭልጋና አካባቢው የነበረውን ሰፊ የኃይል አቅርቦት ችግር ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከአዲስ አበባ በ780 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በጭልጋ ወረዳ በአንጓባ ቡላድጌ ቀበሌ የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት አጠቃላይ አፈጻጸሙ 36 በመቶ ደርሷል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

11 − three =