የአዋሽ II የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከዕቅድ በላይ ኢነርጂ አመነጨ

Published by corporate communication on

የአዋሽ II የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 75 ነጥብ 45 ጌጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ለማምረት አቅዶ 89 ነጥብ 01 ጌጋ ዋት ሰዓት ማመንጨቱን የአዋሽ II እና III የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች  ኃላፊ አቶ ጌታቸው አበበ አስታወቁ፡፡

ኃላፊው እንደገለፁት የአዋሽ III የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግን 92 ነጥብ 29 ጌጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ለማምረት አቅዶ 65 ነጥብ 8 ጌጋ ዋት ሰዓት ማምረት ችሏል፡፡

የአዋሽ III የኃይል ማመንጫ ጣቢያ አፈፃፀም ዝቅ ሊል የቻለው በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ባጋጠመው የጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ ጣቢያው ለአስር ሳምንታት ኃይል ማመንጨት በማቆሙ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

የአዋሽ II የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግን በእንቦጭ ወረርሽኝ ምክንያት ለ1 ወር ኃይል ማመንጨት አቁሞ የነበረ ቢሆንም የዘጠኝ ወር አፈፃፀሙ ግን ከዕቅዱ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

 እንደ ኃላፊው ገለፃ ጣቢያዎቹ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ በእንቦጭ አረም እና በጎርፍ ምክንያት ለተወሰኑ ሳምንታት አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበረ ቢሆንም በተደጋጋሚ በተሰሩ የኦፕሬሽን እና የጥገና ሥራዎች ጣቢያዎቹ  የተሻለ የኤሌክትሪክ ኢነርጂ በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡

የጣቢያው የጥገና ክፍል ኃላፊ አቶ ሮቤል አበበ በበኩላቸው የጎርፍ መከላካያ እና ሌሎች ያልጠናቀቁ ቀሪ የጥገና ሥራዎችን በማከናወን የጣቢያውን ደህንነት ለማስጠበቅ እየተሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የኃይል ማመንጫውን ለማደስ የሚያስችል ጥናት ተጠናቆ ለሥራ አመራሩ ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኃይል ማመንጫ ጣቢያውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች መጀመራቸውን አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡

ጣቢያው የአዋሽ ተፋፈስ አካል ከመሆኑም ባሻገር በጣቢያው ክልል ውስጥ የተለያዩ የዱር አራዊቶች የሚገኙበት ሥፍራ በመሆኑ ለቱሪስት መስህብነት ተመራጭ ሊያደርገው እንደሚችል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የአዋሽ II እና III የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች  እያንዳንዳቸው 32 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አላቸው፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

four − 1 =