የአዋሽ 7 ኪሎ- አሰበ ተፈሪ የማስተላለፊያ መስመር ኢንሱሌተሮችን የመቀየር ሥራ እየተከናወነ ነው

Published by corporate communication on

የአዋሽ 7 ኪሎ – አሰበ ተፈሪ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ኢንሱሌተሮችን የመቀየር ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምስራቅ ሪጅን ትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ እንዳስታወቁት ኢንሱሌተሮቹን መቀየር ያስፈለገው የማስተላለፊያ መስመሩ ከተገነባ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ በመሆኑና ኢንሱሌተሮቹ በእርጅና ምክንያት በመሰባበራቸው ነው፡፡

ኢንሱሌተሮችን የመቀየር ስራው በማስተላለፊያ መስመሩ ላይ ከተተከሉ 3 መቶ 11 ምሰሶዎች (ታወሮች) መካከል በ2 መቶ 62 ምሰሶዎች ላይ እንደሚከናወን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ እስከ አሁን ድረስም በ107 የማስተላለፊያ መስመሩ ታወሮች ላይ 3 መቶ 30 ኢንሱሌተሮችን በአዲስ መተካቱን ገልጸዋል፡፡

በማስተላለፊያ መስመሩ ላይ የነበሩ 786 ፖርሲሊን (porceilin) ኢንሱሌተሮች በአዲስ የፕላስቲክ ኢንሱሌተሮች እንደሚቀየሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሪጅኑ የጥገና ሠራተኞች እየተከናወነ የሚገኘውን ኢንሱሌተሮችን የመቀየር ሥራ እስከ ጥር 2014 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

የአዋሽ 7 ኪሎ – አሰብ ተፈሪ ማስተላለፊያ መስመር 116 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ይህም ከቆቃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ጋር ተገንብቶ ከ1955 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ በጣልያን ኩባንያ የተገነባ ነው፡፡

በተያያዘ ዜና የአዋሽ 7 ኪሎ – አሰበ ተፈሪ ማስተላለፊያ መስመር የመከላከያ ሲስተሙን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡

የመስመሩ የመከላከያ ሲስተም የተጠናከረ ባለመሆኑ ችግር ሲያጋጥመው ሌሎች መስመሮችም አብረዉ ስለሚቋረጡ በችግር ወቅት መስመሩ ራሱን ችሎ የሚቋረጥበት ሁኔታ ለመፍጠር የመከላከያ ሲስተሙን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም በማስተላለፊያ መስመሩ ላይ እየተሰራ ያለውን የማሻሻያ ሥራ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

5 × five =