የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የኃይል ሥርጭትና አቅርቦት ለማሻሻል የሚያግዝ ስምምነት ተፈረመ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭትና አቅርቦት ለማሻሻል የሚያግዝ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ በዋናነት በሀገሪቱ ያለውን የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን አቅም ለማዳበር የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭትና አቅርቦትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩት አስተማማኝና ጥራት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለአምራች ኢንዱስትሪው የጀርባ አጥንት ነው። ስምምነቱ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪው በስፋት ገብተው ዘርፉ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኤክስፖርት ምርት እና ገቢ የሚያሳድጉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ሂደት ውስጥ የሚገጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እና የኃይል አቅርቦት ከመቋረጡ አስቀድሞ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቀነስ ስምምነቱ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል። ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እየቀረበ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በሒደት መሻሻሎችን እያሳየ በመምጣቱ ተቋሙ ሊመሰገን እንደሚገባውም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለይቶ ለሚያቀርባቸው የአምራች ኢንዱስትሪዎች ፣ ለቡሬ፣ ለቡልቡላ፣ ለይርጋለምና ለባዓከር የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
“ከካርቦን ልቀት የፀዳ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል!”
0 Comments