የአሉቶ ጂኦተርማል የማስፋፊያ ፕሮጀክት የእንፋሎት ፍለጋ ቁፋሮው በይፋ ተጀመረ

Published by corporate communication on

የአሉቶ ላንጋኖ የከርሰ ምድር እንፋሎት የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ የእንፋሎት ፍለጋ የጉድጓድ ቁፋሮ በይፋ ተጀመረ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአሉቶ ጂኦተርማል ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ መሳይ ፈቃዱ የቁፋሮ ሥራውን ለማከናወን የሚያስችሉ ቅድመ ሥራዎች በመጠናቀቃቸው እና የሁሉም እቃዎች አቅርቦት፣ የማሽን ተከላ እና ፍተሻ ሥራ በመጠናቀቁ ቁፋሮው ግንቦት 21 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

ቁፋሮውን በሚያዝያ ወር አጋማሽ ለማከናወን ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በውሃ አቅርቦት ማነስና በሌሎች ቀሪ ሥራዎች  ምክንያት መዘግየቱን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

አሁን ግን ችግሮቹን ሙሉ በሙሉ በመቅረፍና ቀሪ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ቁፋሮው በይፋ መጀመሩን  አብስረዋል፡፡

እንደ አቶ መሳይ ገለፃ የእንፋሎት ፍለጋ የጉድጓድ ቁፋሮው ወደ ከርሰ ምድር እስከ 2 ሺህ 700 ሜትር ጥልቀት የሚኖረው ሲሆን የመጀመሪያው 29 ሜትር ቁፋሮ ዛሬ በስኬት ተጠናቋል፡፡

ቁፋሮውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማከናወን ከሚሰራው ሥራ ጎን ለጎን የሰራተኞች መኖሪያ ካምፕ፣ የውሃ አቅርቦት (የውሃ መስመር፣ የፓምፕ ጣቢያና የውሃ ማጠራቀሚያ)፣የክሊኒክ እና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን የመገንባትና አንዳንዶቹንም የማጠናቀቅ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ መሳይ ገልፀዋል፡፡

ፕሮጀክቱን የቻይና ፔትሮሊየም ቴክኖሎጂ እና ልማት ኮርፖሬሽን (CPTDC) የውሃ አቅርቦት ሥራውን፣ የኬንያ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ኩባንያ (KenGen)፣ ኬሩ ኦይል ፊልድ እና ኬሩ መሳሪያዎች( keru oil field & keru equipment) የተባሉ የቻይና ኩባንያዎች የእንፋሎት ፍለጋ የጉድጓድ ቁፋሮውን በጥምረት ሲያከናውኑ የሲቪል ሥራውን ክሮስላንድ የተባለ የሀገር ውስጥ ተቋራጭ እያከናወኑት ይገኛሉ፡፡

ፕሮጀክቱን በፋይናንስ የሚደግፈው በዓለም ባንክ ሲሆን ለግንባታውም 218 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተመድቦለታል፡፡

የአሉቶ ላንጋኖ የከርሰ ምድር እንፋሎት የማስፋፊያ ፕሮጀክት ከ7 ነጥብ 5 ወደ 70 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ታስቦ እየተሰራ ነው፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

20 − nineteen =