የኃይል አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ እና የአሰራር ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያችል ስልጠና ተሰጠ

Published by corporate communication on

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት እና ፓወር አፍሪካ ለ15 የተቋሙ መሃንዲሶች የኤሌክትሮ-ማግኔቲክ ትራንዚየንት ፕሮግራም ሶፍት ዌር ሥልጠና በትብብር ሲሰጡ መቆየታቸውን አስታወቁ፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳምሶን አፅብሃ እንደገለፁት ተቋማቸው በምስራቅ አፍሪካ ለሚገኙ ሃገራት መሰል የኢነርጂ ዘርፉን የሚያግዙ ሥልጠናዎች እና ድጋፎች እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተሰጠው ሥልጠናም የዚሁ ድጋፍ አንድ አካል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናውን ላጠናቀቁ የተቋሙ ሠራተኞች የምስክር ወረቀት የሰጡት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዋና ሥራ አስፈፃሚ ቴክኒካል አማካሪ አቶ አንዳርጌ እሸቴ በበኩላቸው ሥልጠናው በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና በብሔራዊ የኃይል ቋት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና የአሰራር ሥርዓቱን ለማዘመን እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ አንዳርጌ ገለፃ በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ ችግሮች የኃይል መቆራረጥ እንደሚከሰት አስታውሰው ሥልጠናው ይህን ችግር ከመቅረፍ አኳያ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል፡፡

ኤሌክትሮ ማግኔቲክ ትራንዚየንት ፕሮግራም ሶፍት ዌር የኃይል ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ከመከናወናቸው በፊት ለግንባታው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ቅድመ ትንታኔ በመስራት የዕቃዎቹን አይነት እና ጥራት ለመፈተሽ ይጠቅማልም ተብሏል፡፡

ሶፍትዌሩ በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ተፈጥሯዊ እና ሠው ሰራሽ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ቴክኒካዊ ትንታኔ በመስራት ችግሩን ለመለየት እና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝ ከሥልጠናው ተሳታፊዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

1 × 3 =