የኃይል ሽያጭ ስምምነት ተደረገ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል ሽያጭ ስምምነት አደረጉ፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ እና የኢትየጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈረው ተሊላ ተፈራርመዋል፡፡
ትናንት በተካሄደው የፊርማ ሥነ-ስርዐት ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ እንደተናገሩት ስምምነቱ ተቋማቱ በተሻለ መንገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና የጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡
ተቋማቱ በኃይል ኔትወርክ የተገናኙ እንደመሆናቸው ስምምነቱ ያላቸውን ቅንጅትና ትብብር የበለጠ ለማጠናከር እና የስራ አፈጻጸማቸውን ለማሻሻል የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈረው ተሊላ በበኩላቸው መስሪያ ቤቶቹ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በህግ በተወሰነው አግባብና በስምምነታቸው መሰረት እንዲወጡ እንደሚያስችላቸው ነው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማርኬቲንግ እና ገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ታምራት እንደተናገሩት ስምምነቱ የሁለቱ ተቋማትን የኤሌክትሪክ ግብይት በህግ አግባብ ለማከናወን ያስችላቸዋል፡፡
በተቋማቱ መካከል ቀደም ሲል የነበረው የኤሌክትሪክ ግብይት በ40/60 ሽያጭ ስምምነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን የአሁኑ ስምምነት ግን የቀድሞውን አሰራር በመለወጥ በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች በሚገጠም ቆጣሪ ንባብ ላይ ተመስርቶ የሚከናወን ይሆናል፡፡
0 Comments