የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹን ከእንቦጭና ጎርፍ ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች ተሰርተዋል

በተያዘው በጀት ዓመት የአዋሽ II እና III የውኃ ሃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ከእንቦጭ እና ጎርፍ ለመታደግ የቅድመ መከላከል ሥራዎች መሰራታቸው ተገለፀ፡፡
የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው አበበ እንደገለፁት ክረምቱን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ መከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
በአዋሽ II ማመንጫ ጣቢያ ወደ ተርባይኑ የሚገባው ውኃ በእንቦጭ አረም እንዳይዘጋ የሚያግዝ መከላከያ መሰራቱን የገለፁት አቶ ጌታቸው በአዋሽ III ማመንጫ ጣቢያም ጎርፍ ወደ ኃይል ማመንጫ ቤት (Power House) በመግባት ጉዳት እንዳያደርስ የሚያስችል ግንባታ መሰራቱን አብራርተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ክረምት ተከስቶ የነበረው ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ በአዋሽ III የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ ጉዳት ማድረሱ የሚታወስ ነው፡፡ ጣቢያውን ወደ ማመንጨት ሥራው ለመመለስ በተደረገው ርብርብ ወደ ሥራ ከተመለሰ በኋላ በበጀት ዓመቱ 96 ነጥብ 6 ጊጋ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ ማመንጨቱን አቶ ጌታቸው ገልፀዋል፡፡
በተያያዘ በጣቢያዎች ላይ የአረንጓዴ ልማትን ተግባራዊ ለማድረግ በተያዘው እቅድ በአዋሽ II እና III የውኃ ሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች 485 ሺህ ብር በሆነ ወጭ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሀገር በቀልና የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
0 Comments