የችግኝ ማፍላትና ተከላ በኃይል ማመንጫዎችና በፕሮጀክቶች በመካሄድ ላይ ነው

Published by corporate communication on

የአሉቶ ጆኦተርማል የማስፋፊያ ፕሮጀክት ችግኝ በማፍላትና በመትከል የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን የፕሮጀክቱ የአካባቢና ማህበረሰብ ተፅዕኖ ክትትል ክፍል አስታወቀ፡፡

የፕሮጀክቱ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ አየለ ባንጃው እንደገለፁት በፕሮጀክቱ የመድሃኒትነት ይዘት ያላቸው እንደ ሞሪንጋና ትሩኒም፣ ለደን ልማት የሚያገለግሉ እንደ ጀካራንዳ፣ ሸውሸዌና ግራር ያሉ፣እንዲሁም ለምግብነትና ለአፈር ጥበቃ የሚውሉ ችግኞች እየፈሉ ነው፡፡

እስካሁንም በፕሮጀክቱ በ2012 ዓ.ም 60 ሺህ፣ በ2013 ደግሞ 55 ሺህ ችግኞች መፍላታቸውን ባለሙያው ገልፀዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ከለሙት ችግኞች መካከል ለሞጆ – ዝዋይ የፍጥነት መንገድ ከ20 ሺህ በላይ፣ ለዝዋይ ፌደራል ማረሚያ ቤት ከ15 ሺህ በላይ፣ ለአካባቢው ነዋሪዎች ከ10 ሺህ በላይ የተሰራጩ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በፕሮጀክቱ እየተተከሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደባለሙያው ማብራሪያ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ሙቀትና የሚሸረሸር አፈር ያለበት አካባቢ በመሆኑ ድርቅን ተቋቁመው አፈርን ለመጠበቅ የሚያስችሉ የዕጽዋት ዓይነቶች ትኩረት ተሰጥቷቸው ተተክለዋል፡፡

የተተከሉት ችግኞች እንዲፀድቁ ክትትል እየተደረገ ሲሆን በ2012 ከተተከሉት ውስጥ የፀደቁት ከ60 በመቶ በላይ መሆናቸውን ባለሙያው ገልፀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጢስ አባይ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በጨረጨራ ግድብ አጠገብ ከ650 በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን ተከላ አከናውኗል፡፡

ጣቢያው ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ያገኛቸውን ችግኞች ዓባይ ከጣና ተለይቶ በሚወጣበት የጨረጨራ ግድብ አቅራቢያ ተክሏል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

six − 2 =