የታርጫ ባለ 132/33 ኪ.ቮ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ተጀመረ

Published by corporate communication on

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን ታርጫ ዙሪያ ወረዳ የባለ 132/33 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ተጀምሯል፡፡

በወረዳው አባ ዳሂ ቀበሌ በ1998 ዓ.ም. ተገንብቶ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የአባ ባለ 132/33  ኪ.ቮ. ማከፋፈያ ጣቢያ በደረሰበት የመሬት መንሸራተት ጉዳት የተነሳ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት በማቋረጡ በወረዳው ጎሪቃ ቤርሳ ቀበሌ አዲስ ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

የግንባታው የሲቪል ሥራዎች ኃላፊ አቶ በላይ ሀብተገብርኤል እንደገለጹት ግንባታው በይፋ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የማከፋፈያ ጣቢያው የመሰረት ሥራ 80 በመቶ፣ የትራንስፎርመር ማስቀመጫ የመሰረት ግንባታ 90 በመቶ ተከናውኗል፡፡

የሠራተኞች የመኖሪያ ቤት የቅየሳ ሥራ መከናወኑንና አጠቃላይ የሲቪል ሥራው 23 በመቶ መድረሱን አቶ በላይ ገልፀዋል፡፡

በአካባቢው እንደ ድንጋይ፣ አሸዋና ጠጠር ያሉ የግንባታ ግብዐቶች እጥረት ቢኖርም ግንባታውን ከዓመት ባነሰ ጊዜ ለማጠናቀቅ ይሰራል ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች አስተባባሪ አቶ ደምረው ታደሰ በበኩላቸው የሲቪል ሥራዎችን ተከትሎ የኤሌክትሮ መካኒል ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የመሬት መንሸራተት ከገጠመው ማከፋፈያ ጣቢያ የኤሌክትሮ መካኒካል ዕቃዎችን በጥንቃቄ በመፍታት አጓጉዞ በአዲሱ ማከፋፈያ ጣቢያ ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

ይህም ፕሮጀክቱ በፍጥነት ለማጠናቀቅ ዕድል ይሰጣል ያሉት አቶ ደምረው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች አፈፃፀም 10 ነጥብ 15 በመቶ መድረሱን ገልፀዋል፡፡

በማከፋፈያ ጣቢያው ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ደመላሽ ዳምጠውና ማርታ ከበደ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ ወጣቱ ተወልዶ ባደገበት መንደር የሥራ ዕድል መፈጠሩ ሥራ ለማግኘት ወደሌላ አካባቢ መጓዝን ያስቀራል ብለዋል፡፡

በሚነሳው እና አዲስ በሚገነባው ማከፋፈያ ጣቢያ ዙሪያ ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከታርጫ ዙሪያ ወረዳ አመራሮች ጋር ውይይቶች ተደርገው ለፕሮጀክቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ጥበቃ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡

በአባ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ቀደም ሲል ከማከፋፈያ ጣቢያው ኃይል ሲያገኙ የነበሩ አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በጊዜያዊነት በማቋቋም አገልግሎቱን ሲያገኙ ቆይተዋል፡፡

አዲሱን ማከፋፈያ ጣቢያ የሚገነባው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የራስ ኃይል ቢሮ ሲሆን ለሥራው ከ65 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ተመድቦለታል፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው 5 ወጪ መስመሮች ያሉትና አንድ ባለ 20/25 MVA ትራንስፎርመር ይኖሩታል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

5 × two =