የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያውያን ህልውና መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ

Published by corporate communication on

የታላቁ ኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያውያን ህልውና መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።    

የግድቡን ግንባታ አስመልክቶ በስካይላይት ሆቴል በተዘጋጀ ሀገር አቀፍ ሲምፓዚየም  ላይ  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት  የዓባይ ተፋሰስ የሃገሪቱን ሁለት ሶስተኛውን የውሃ ተፋሰስ የሚሸፍን በመሆኑ ዓባይን የማልማት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው።

ግድቡ መላው ኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብታቸውን ያፈሰሱበት የቀጣይ ልማት የጀርባ አጥንት ሲሉ ገልፀውታል።   

የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጐል በርካታ ዘመቻዎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን የገለፁት አቶ ደመቀ  ይህን ሴራ ለማክሸፍ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ሊቆም ይገባል ብለዋል።

 የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው  ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ  ላይ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የጋራ ተጠቃሚነትን እንደምታከብር ተናግረዋል።

በቀጣዩ ክረምት ቀጠሮ የተያዘለት ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት እንደማይራዘም ገልፀዋል።

 የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ደግሞ የግድቡ የሲቪል ሥራዎች 91 በመቶ እንዲሁም የብረታብረት ሥራዎች 53 ነጥብ 7 በመቶ መከናወናቸውንና አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 79 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል።

 የሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ለማሳካትም በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው ኢንጂነር ክፍሌ የተናገሩት።    

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሽብር ባልቻ የግድቡን ግንባታ በተያዘለት የጊዜ መርሐ ግብር ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቦርድ አባላት፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር÷ የተቋሙ አመራሮች እና ሠራተኞች የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

 በሲምፖዚየሙ ላይ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ የተካሄዱ ታሪካዊ፣ ህጋዊ እና ስነ ምህዳራዊ ጥናቶች በተለያዩ ምሁራን በመቅረብ ላይ ናቸው።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

9 − two =