የተቋረጠውን የዋግ ኽምራ ዞን ኤሌክትሪክ ለማገናኘት እየተሰራ ነው

Published by corporate communication on

በዋግ ኽምራ ዞን በሚገኙ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎትመልሶ ለማገናኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሰሜን ምስራቅ ሪጅን ትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ዳይሬክተር አቶ ታገል ደገፉ እንደገለፁት በአካባቢው  ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ኤሌክትሪክ የተቋረጠው በሶስት የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ ስርቆት በመፈፀሙና በመውደቃቸው ነው።

ወደስፍራው ለጥገና የተንቀሳቀሰው ቡድን የወደቁትን ምሰሶዎች መልሶ ለመትከል ከእሁድ ጀምሮ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

ከአንድ ወር በፊት ከአላማጣ እስከ ሰቆጣ በሚገኙት 269 ምሰሶዎች ላይ የፍተሻ ስራ መከናወን መጀመሩን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በስምንት የብረት ምሰሶዎች ላይ የስርቆት ሙከራ መፈፀሙን በማረጋገጥ ምሰሶዎቹ ከመውደቃቸውና ኤሌክትሪክ ከመቋረጡ  በፊት መስተካከሉን ገልፀዋል።

በአሁኑ የተፈፀመው  ስርቆት በመስመሩ ውስጥ በሚገኙትና የፍተሻ ስራ ባልተካሄደባቸው 47 ምሰሶዎች ውስጥ በሶስቱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የደረሰውን ችግር በተመለከተም ለዞኑ አስተዳደር የማሳወቅ ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል።

በምሰሶዎቹ መውደቅ የዞኑ ዋና ከተማ ሰቆጣን ጨምሮ በአምደወርቅ፣ በዳህና፣በአበርገለ፣ በሰሀላ፣በዝቋላና በአካባቢያቸው ኤሌክትሪክ ተቋርጧል።

የዋግ ኽምራ ዞነ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ኃይል የሚያገኙት ከአላማጣ ባለ 66 ኪሎቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ከሚወጣ መስመር ነው።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

five + twelve =