የተቋም ሀብት ዕቅድ ስርዓት – ERP ሥርዓት በይፋ መተግበር ጀመረ

Published by corporate communication on

በተቋሙ በተመረጡ አምስት ዘርፎች የተዘረጋው የተቋም ሀብት ዕቅድ ሥርዓት – ERP ሥርዓት  የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቆ በይፋ መተግበር ጀመረ፡፡

የተዘረጋውን ሥርዓት የያስጀመሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ ተቋሙ ግዙፍ ሀብትን የሚያንቀሳቅስ ቢሆንም አሰራሮቹ በሲስተም ያልተደገፉ እና መረጃዎች ወረቀት ተኮር እንደነበሩ ገልፀዋል፡፡

ስለሆነም ተቋሙን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር አስፈላጊ በመሆኑ የተቋም ሀብት ዕቅድ ሥርዓት (Enterprise resource planning) ትግበራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተደረገ ሥምምነት የተጀመረው የSAP_ERP ሲስተም ዝርጋታ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቆ ሥራ መጀመሩን ያበሰሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሥራው ላይ የተሳተፉትን አመራሮችና ባለሙያዎችን አመስግነዋል።

በቀጣይም ተቋሙ ሌሎች ቴክኖሎጅዎችን ተግባራዊ በማድረግ ዛሬ ከተዘረጋው ሲስተም ጋር አስተሳስሮ ለመስራት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

የተቋሙ የሞደርናዜሽን ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ገነቱ ደሳለኝ በበኩላቸው ተቋሙ ከኢትዮጰያ አየር መንገድ እና ሳፕ (SAP) ከተባለ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ጋር በመተባበር በሦስት ደረጃዎች የተቋም ሀብት ዕቅድ ሥርዓት ለመዘርጋት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

የተቋም ሀብት ዕቅድ ሥርዓት (Enterprise resource planning) ተግባራዊ መደረጉ ተጠያቂነት ያለው ሥርዓትን ለመዘርጋት፣ በተቋሙ ያሉ የሥራ ክፍሎችን ለማስተሳሰር እና ወጥነት ያለው ሥራ ለማከናወን የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሲስተሙን ለመዘርጋትና ለሥልጠና 143 ሚሊዮን ብር SAP የተባለውን ሲስተም ከነፍቃዱ ለመግዛት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዩሮ ወጭ መደረጉን አቶ ገነቱ አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሜሪሻል ቺፍ ኦፊሰር አቶ ኢሳያስ ወ/ማርያም በበኩላቸው ሲስተሙ ዘመናዊ ከሚባሉት መካከል ቀዳሚው መሆኑን ጠቅሰው ድርጅታቸው ቀሪ ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

four + twenty =