የተቋሙ 191 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ዕዳ ተሰርዞ ወደ ካፒታል እንዲዞር ተደረገ

Published by corporate communication on

መንግስት ከፍተኛ ዕዳ ያለባቸው የልማት ድርጅቶች ዕዳ እንዲሰረዝና ወደካፒታል እንዲዞር ባሳለፈው ውሳኔ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወሰደው ብድር ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው ዕዳ ተሰርዞ ወደ ካፒታል እንዲዞርለት ተደረገ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የመንግስት ዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዛሬ ባደረጉት የአራትዮሽ ስምምነት ተቋሙ እ.ኤ.አ. ከ2004 እስከ 2016 ከንግድ ባንክ የወሰደው ብድር ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በ2017 የወሰደው ብድር በከፊል ወደ ካፒታል እንዲዞርለት ተወስኗል፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቋሙ የወሰዳቸው ቀሪ ብድሮችን ግን በራሱ የሚከፍል ይሆናል፡፡

የዕዳ ስረዛው ተቋሙን 191 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ከነወለዱ የሚያስቀርለት ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት 17 ነጥብ 25 ቢሊየን ብር እንዲሁም በቀጣይ በጀት ዓመት 18 ነጥብ 81 ቢሊየን ብር ወለድ ከመክፈል ታድጎታል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ይከፈል የነበረው የ17 ነጥብ 25 ቢሊየን ብር ወለድ የተቋሙን የ2013 በጀት ዓመት ገቢ ከ85 በመቶ በላይ ይሸፍናል፡፡

የዕዳ ስረዛው የተቋሙን ዕዳ ወደ ካፒታልነት ስለሚያዞረው የሂሳብ መዝገቡን በማስተካከል ወደ ጤነኛነት የሚመልሰው ይሆናል፡፡

ጠንካራና ተወዳዳሪ ተቋም በማድረግም ወደፊት ለሚያከናውናቸው ሥራዎች አቅም ይፈጥርለታል፡፡

በስምምነቱ መሰረት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተሰጠው ብድር ወደካፒታል በመዞሩ አበዳሪው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 191 ነጥብ 8 ቢሊየን ብሩን የሚጠይቀው ከተቋሙ ላይ ሳይሆን አዲስ ከተቋቋመው የመንግስት ዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ላይ ይሆናል፡፡

ከፍተኛ ዕዳ ካለባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የስኳር ኮርፖሬሽን፣ የቀድሞ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የኬሚካል ኢንደስትሪ፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኢትየጵያ አገልግሎት ዕዳ እንዲሰረዝ የሚያደርግ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

8 − five =