የተቋሙ የ2013 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2014 ዕቅድ ተገመገመ

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የ2013 በጀት ዓመት አፈፃፀሙንና የ2014 በጀት ዓመት ዕቅዱን በአዳማ ከተማ ለሶስት ቀናት ገምግሟል።

በግምገማው ላይ ሁሉም የስራ ሂደት ሥራ አስፈፃሚዎችና የዋና ስራ አስፈፃሚ ተጠሪ መምሪያ ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል።

 የ2013 በጀት ዓመት አፈፃፀም በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈ ቢሆንም አበረታች ውጤት የተመዘገበበት እንደነበር ተጠቅሷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት  ላይ በተደጋጋሚ የደረሰውን ውድመት በማስተካከል ህብረተሰቡ አሌክትሪክ እንዲያገኝ የተሰራው ሥራ ለአብነት ተነስቷል።

በዚህም ተቋሙ ከ5 መቶ ሚሊየን ብር የሚበልጥ ጉዳት ቢያጋጥመውም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በማለፍ አበረታች ስራ መስራቱ ተገልጿል።

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን የሚያስችሉና  አስቀደመው ኃይል የሚያመነጩትን ሁለት ዩኒቶች ዝግጁ ለማድረግ  የተሰሩት ስራዎችም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷቸው የተከናወኑ እንደነበር ተመላክቷል።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶችም ኤሌክትሪክን በፍትሐዊነት ለማዳረስ የተጀመረውን ሀገራዊ ጥረት በሚያሳካ  ደረጃ መከናወናቸው ተነስቷል።

ሌሎች የኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶችም በአብዛኛው ጥሩ አፈፃፀም እንደነበራቸው ተገምግሟል።

ለመጠናቀቅ የተቃረቡትንም በትኩረት በመስራት በተያዘው በጀት ዓመት አጠናቆ ወደስራ ለማስገባት  አቅጣጫ ተቀምጧል።

የተቋሙ ገቢና የፋይናንስ ሁኔታ ከዓመት ዓመት እየተሻሻለና ጤናማ እየሆነ መምጣቱ  የተጠቀሰ ሲሆን ከሀገር ውስጥ የኃይል ሽያጭም ሆነ ከኤክስፖርት የተሻለ ገቢ የተገኘበት ዓመት በመሆኑ ልምድ ሊወሰድበት ይገባል ተብሏል።

ለሀገር ወስጥ ኃይል ሽያጭ ገቢ ማደግ የስማርት ሜትሮች በሁሉም ኃይል ማመንጫዎችና የፀጥታ ችግር ካለባቸው አካባቢዎች በቀር በሁሉም ማከፋፈያ ጣቢያዎች መተከሉ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

የሲስተም ጥናት መደረጉ፣ የኤሌክትሪክ ዘርፍ የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ መጠናቀቁ፣ የ25 ዓመት ማስተር ፕላን መዘጋጀቱና ለተመረጡ ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት መዘጋጀቱ በአበረታች የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።

የበጀት አፈፃፀሙን የገመገመው ማኔጅመንቱ አፈፃፀሙ አበረታች መሆኑን አንስቷል።

ማኔጅመንቱ  የ2013 በጀት ዓመት ላይ የነበሩ የአፈፃፀም ክፍተትና ጥንካሬዎችን በመለየት የተዘጋጀውን የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ በጥልቀት ገምግሟል።

በሁሉም የስራ ክፍሎች የታቀደው ዕቅድ ከዘርፉ መሪ ዕቅድ ተመንዝሮ የቀረበ መሆኑን በማረጋገጥ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ሠራተኛና አመራር በትጋት እንዲንቀሳቀስ አሳስቧል።

ከግምገማው በኋላ ማኔጅመነቱ የአዳማ አንድ እና ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫዎችን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

14 + 1 =