የተቋሙ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች “የነጩ ፖስት ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግስት” ዘመቻን ተቀላቀሉ

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች “የነጩ ፖስት ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግስት” በሚል ርዕሰ ጉዳይ በሃገር ዓቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ ንቅናቄ በዛሬው ዕለት በይፋ ተቀላቅለዋል፡፡

የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች በሃገራዊ ዘመቻው ላይ በመሳተፋና በደብዳቤው ላይ ፊርማቸውን በማኖር የኢትዮጵያን የተደበቀ እውነታ ለአለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንዲታወቅ ለማድረግ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡

በንቅናቄ ዘመቻው ላይ የተሳተፉት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቴክኒካል አማካሪ አቶ አንዳርጌ እሸቴ እንደተናገሩት የንቅናቄ ዘመቻው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች እያደረሰ ያለውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ያግዛል ብለዋል፡፡

“የነጩ ፖስት ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግስት” የንቅናቄ ዘመቻ ህብረተሰቡ የሃገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየት እድል እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ አንዳርጌ ገለፃ ዘመቻው ኢትዮጵያ ተበዳይ ሆና ሳለ በተቃራኒው በሃገሪቱ ያለውን እውነታ በማዛባት ጫና ለማሳደር የሚፈልጉ የተለያዩ ኃይሎችን በመታገል የሃገሪቱን መፃኢ ዕድል ለመወሰን ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

የንቅናቄ መድረኩ በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ተጨባጭ መረጃ ለነጩ ቤተ መንግስት ብቻ ሳይሆን መላው ዓለም እውነቱን እንዲገነዘብ ለማድረግ እንደሚረዳም የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ተናግረዋል፡፡

የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ከመሯሯጥ ይልቅ የህወሓትን ሴራ በማጋለጥ ከህዝባችን ጎን ሊቆም እንደሚገባም ነው ሠራተኞቹ የጠቆሙት፡፡

የወገኑን ሞትና መፈናቀል የማይፈልግ ኢትዮጵያ የሆነ ሁሉ የንቅናቄ ዘመቻውን በመቀላቀል ኢትዮጵያን የመበተን ፍላጎት ያለው የህወሓት ቡድን በሃገሪቱ ላይ እየፈጸመ ያለውን ተግባር ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት እንደሚገባ የተቋሙ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች አሳስበዋል፡፡

መስከረም 3 ቀን 2014 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው “የነጩ ፖስት ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግስት” ሃገራዊ ዘመቻ እስከ መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

11 + seven =