የተቋሙን የብድር ዕዳ ጫና ለማቃለል እየተሰራ ነው

Published by corporate communication on

የተቋሙን የብድር ጫና ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ አስታወቁ፡፡

ሥራ አስፈፃሚው እንዳስታወቁት ተቋሙ የተሰጡትን ተልዕኮዎች ለመወጣት ከተለያዩ የፋይናንስ ምንጮች በመደበኛ የወለድ ምጣኔ የሚገኙ ብድሮችን (Commercial loan) እና አነስተኛ የወለድ ምጣኔና ረዘም ያለ የመክፈያ ጊዜ ያላቸው ብድሮችን (Concessional loans) በመጠቀም የተለያዩ የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ይሁንና ተቋሙ እንደ ሀገር ለሚከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በሌሎች ተቋማት ስም በመደበኛ የወለድ ምጣኔ የሚገኙ ብድሮችን በመውሰድ የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ይህም የተቋሙን ብድር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲንር አድርጎታል፡፡

የተቋሙ የብድር ጫና በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ሁኔታ ለሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት በማስረዳት የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች እየተወሰደ መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡

እንደ ሀገር የብድር ጫናን ለማቃለል ብድሮቹ እንዲሰረዙ ወይም በአነስተኛ የወለድ ምጣኔና በረዥም የመክፈያ ጊዜ እንዲከፈሉ ለማድረግ በመንግስት በኩል ከአበዳሪ ተቋማት ጋርም ውይይት ሲደረግ እንደነበር ይታወሳል፡፡

እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ከነበረው የድርጅቱ ጠቅላላ ብድር ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነውን ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ለማዞር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ ሲሆን ይህም የተቋሙን የብርድ ጫና ለመቀነስ የራሱ የሆነ አስዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ለኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግንባታ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል በመልሶ ማበደር የተገኙ 20 የብድር ውሎች ከነወለዳቸው ወደ ተቋሙ ካፒታል እንዲዞሩ ተደርጓል፡፡

በዚህም በመልሶ ማበደር የተገኘ ከ48 ቢሊየን ብር በላይ ወደ ተቋሙ ካፒታል የማዞሩ ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪውን ብድር ተቋሙ ወደ ስራ አስገብቶ ሲጠቀምበት ተጨማሪ ካፒታል እንዲሆንለት በተወሰነው መሰረት በ2012 በጀት ዓመት ከ 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ በመጠቀም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተጨማሪ ካፒታል የተደረገ ሲሆን በድምሩ ከ 56 ቢሊየን ብር በላይ የተቋሙ ዕዳ እንዲቀንስና ካፒታሉ በዚሁ ልክ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡

የተቋሙን የብድር ጫና በመፍታት ጤናማ የፋይናንስ ቁመና እንዲኖረው ለማድረግ ሁሉም ሰራተኛ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል፣ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚወጣውን ወጪ በመቀነስና በየክፍሉ የሚገኙ መልካም ሁኔታዎችን ወደ ገቢ በመቀየር እንዲሁም ፕሮጀክቶች ተጨማሪ ወጪ ሳይጠይቁ በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አቶ ደመረ ጠይቀዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

eight − five =