የባህር ዳር-ወልድያ -ኮምቦልቻ ከፍተኛ የኃይል መስመር ፕሮጀክት ግንባታ እየተከናወነ ነው

የባህር ዳር-ወልድያ -ኮምቦልቻ ከፍተኛ የኃይል መስመር ፕሮጀክት ከሚኖሩት የባለ 400 ኪ.ቮ 831 የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ውስጥ የ790 ምሰሶዎች የመሰረት ግንባታ ሲጠናቀቅ 500 ምሰሶዎችን የመትከል ስራ መከናወኑን የፕሮጀክት ሳይት ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ተሾመ ገለፁ፡፡
መሐንዲሱ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ 28 ኪ.ሜ የሚሸፍን ተጨማሪ የባለ 230 ኪ.ቮ ተሸካሚ 64 ታወሮች የመትከልና ሽቦ የመዘርጋት ሥራዎችን ያጠቃልላል፡፡
ፕሮጀክቱ ከነባሩ ባህር ዳር ቁጥር 2 ማከፋፈያ ተነስቶ 381 ኪ.ሜ በመሸፈን አዲስ ወደሚገነቡት የወልዲያ እና የኮምቦልቻ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚደርስ ነው፡፡
እንደ ሳይት መሐንዲሱ ገለፃ የመስመር ዝርጋታውን ለማከናወን ከሚያስፈልጉት የኤሌክትሮ መካኒካል ዕቃዎች ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ ሳይት የደረሱ ሲሆን ቀሪዎቹም ወደብ ደርሰዋል፡፡
የግንባታውም አማካይ አፈጻጸምም ከ60 በመቶ በላይ መድረሱን አስተባባሪ መሐንዲሱ ተናግረዋል፡፡
የመስመር ዝርጋታ ግንባታ ስራውን ታታ ፕሮጀክት ሊሚትድ የተባለ የህንድ ኩባኒያ የሚያከናውን ሲሆን አማካሪው ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ነው፡፡
በ2010 ዓ.ም. የተጀመረውን ይህን ፕሮጀክት በ18 ወራት ለማጠናቀቅ ታቀዶ የነበረ ቢሆንም የኮረና ቫይረስ ወረርሽን ተጽእኖ ፣130 ታወሮች የተለያዩ ክፍሎች ላይ የስርቆት ወንጀል መፈጸሙ እና ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች እየተፈጠረ ያለው ጉዳት ፕሮጀክቱን ለተጨማሪ ጊዜና የገንዘብ ወጪ ዳርጎታል፡፡
የመስመር ዝርጋታውን ስራ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ወጪው ሙለ ለሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተበጅቶለታል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የክልሉን ፍትሃዊ የኃል አቅርቦት ጥያቄ በመመለስ በኩል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል፡፡
0 Comments