የቡኢ ባለ 132/33/15 የማከፋፈያ ጣቢያ ተመረቀ

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በጉራጌ ዞን የተገነባው የቡኢ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ዛሬ በይፋ ተመረቀ፡፡
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ርዳው፣ የፊደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቴ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የፌደራል፣ የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ማከፋፈያው ለተጀመሩም ሆነ አዲስ ለሚጀመሩ ኢንቨስትመንቶች አስተማማኝ የኃይል ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል፡፡
እንደዚህ ያሉ ፕሮጀክቶች የክልሉን ልማት የሚያፋጥኑ በመሆናቸው ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በበኩላቸው የማከፋፈያው መገንባት ቀደም ሲል በከተማዋ የተለያዩ የልማት ስራ ለመስራት እቅድ ያላቸውን የአካባቢው ተወላጆች እንደሚያበረታታ ተናግረዋል፡፡
የቡኢ ከተማ ከንቲባ አቶ ዘመቻ እንዳለ ደግሞ ከተማዋ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ እንደመሆኗ የማከፋፈያ ጣቢያው መገንባት አዳዲስ ባለሃብቶችን በመሳብ ረገድ የላቀ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው አለው ብለዋል፡፡
በምርቃት ስነሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ የማከፋፈያ ጣቢያው ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 7 ነጥብ አንድ ሚሊየን ዶላር ብድርና ከመንግስት በተገኘ 39 ሚሊየን 320 ሺህ 425 ብር በጀት መገንባቱን ተናግረዋል፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያው አራት ባለ 33 ኪሎ ቮልት እና አራት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ያሉት ሲሆን ቡኢ ከተማን ጨምሮ 22 ከተሞችንና የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ተደራሽ ያደርጋል።
የማከፋፈያ ጣቢያውን ገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ያደረገው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኮንስትራክሽን የራስ አቅም(Own force ) ቢሮ ነው፡፡
0 Comments