የቆቃ ሐይቅን ከእምቦጭ አረም ለመታደግ የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

Published by corporate communication on

የቆቃ ሐይቅን ከእምቦጭ አረም ለመታደግ በሚደረገው ዘመቻ የቆቃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ አመራሮች እና ሠራተኞች በምስራቅ ሸዋ ዞን ሊሞ ወረዳ ቆቃ ነገዎ ቀበሌ በመገኘት ተሳትፎ አደረጉ፡፡

የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መለስ ሲሎ እንደገለፁት የዘመቻው ዋና ዓላማ መጤ አረሙ በሐይቁና በግድቡ ላይ እያሳደረ የሚገኘውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ነው፡፡

በዕለቱም አንድ ሔክታር የሚሸፍን የእምቦጭ አረም የመንቀል እና ለአረሙ ምቹ የሆኑ ደለሎችን የማፅዳት ሥራ መከናወኑንም ነው የጣቢያው ኃላፊ የተናገሩት፡፡

በሐይቁ ላይ የእምቦጭ አረም በፍጥነት እየተስፋፋ የሚሄድ ከሆነ ወደ ግድቡ የሚገባውን የውሃ መጠን በመቀነስ የሚመረተውን ኃይል  ሊቀንስ ይችላል ሲሉም ኃላፊው ተፅዕኖውን ገልፀዋል፡፡

ከ50 በላይ የጣቢያውን ሠራተኞች ያሳተፈው ዘመቻ የመጤ አረሙን የመስፋፋት ጉዞ ለመግታት ያለመ ቢሆንም ችግሩ አሳሳቢ ከመሆኑ አንፃር  ድጋፉ እና ርብርቡ መቀጠል እንዳለበት  አቶ መለስ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ልዩ ትኩረት በመስጠትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ ሐይቁን እና የኃይል ማመንጫ ግድቡን ከመጤ አረም  ለመታደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የቆቃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከ 60 ዓመት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

የሊሞ ወረዳ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ገነሞ ኤሚ በበኩላቸው ወረዳው የጀመረውን እምቦጭን የማጥፋት ዘመቻ በመደገፍ የቆቃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ አመራሮች እና ሠራተኞች ተሳትፎ በማድረጋቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

1 × five =