የሻምቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክት ግንባታን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው

Published by corporate communication on

ባለ 230 ኪ.ቮ የሻምቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ግንባታን በተያዘለት የጊዜ መርሀ ግብር ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚኒልክ ሠለሞን ተናገሩ፡፡ ፕሮጀክቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 16 ወራት እንደሚወስድ ዕቅድ ተይዞለታል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራትም የቢሮና የመኖሪያ ቤቶች፣ የተለያዩ ዕቃዎች እና የትራንስፎርመር የመሰረት ቆፋሮ የተጠናቀቁ ሲሆን የፋውንዴሽን አርማታ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የሳይት ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡

ሻምቡ ከተማ ዳርቻ፤ በዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ የሚገኘው የሻምቡ ባለ 230/33 ኪ.ቮ የኃይል ማከፋፍያ ጣቢያ አንድ ገቢ እና ስድስት ወጪ መስመሮች የሚኖሩት ይሆናል፡፡

 እንደ አቶ ሚኒልክ ገለፃ ፕሮጀክቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ አራት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እና ሶስት ሚሊዮን ብር የተበጀተለት ሲሆን ከዚህም ውስጥ 85 በመቶው ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር እንዲሁም 15 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ነው፡፡ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ለመቶ ያህል የአካባቢው ነዋሪዎችም ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

ፕሮጀክቱን የቻይናው ሲኖ ሃይድሮ ኩባንያ በዋና ተቋራጭነት፤  ሃገር በቀሉ መላ ኢንጂነሪንግ ደግሞ የሲቪል ሥራውን በንዑስ ተቋራጭነት፤ የጣሊያኑ ኢ.ኤል.ሲ ኤሌክትሮ ኮንሰልታንት በበኩሉ የማማከር ሥራውን ወስዶ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ አቶ ሚኒልክ አስታውቀዋል፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅ 63 ኤም ቪ ኤ አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች የሚተከሉለት ይህ ማከፋፈያ ጣቢያ ለአካባቢው ማህበረሠብ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ነው የሳይት ስራ አስኪያጁ ያስረዱት፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

13 + 19 =