የሻምቡ የኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክት የፍተሻና ሙከራ ሥራ በመከናወን ላይ ነው

Published by corporate communication on

የሻምቡ ባለ 230 ኪ.ቮ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክት አብዛኛዎቹ የሲቪልና ኤሌክትሮ-ሜካኒካል ሥራዎች ተጠናቀው የፍተሻና ሙከራ ሥራ መጀመሩን የፕሮጀክቱ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ሙሉብርሃን ተናግረዋል፡፡

ተወካዩ እንደገለፁት የፕሮጀክቱ አማካይ አፈፃፀም 92 በመቶ የደረሰ ሲሆን አጠቃላይ ሥራውን በቀጣዩ ወር በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

እያንዳንዳቸው 31 ነጥብ 5 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፈርመሮች፣ የኃይል መቆጣጠሪያ ክፍል እና ከኤሌክትሪክ መቆጣጠሪያ ስርዓት ጋር የሚገናኘው የባስባር ገጠማ ሥራዎች መጠናቀቃቸውንም ነው ተወካይ ኃላፊው የገለፁት፡፡

በተጨማሪም ከፊንጫ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ሻምቡ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ ለመዘርጋት ከታቀዱት 83 የኃይል ተሸካሚ ማማዎች መካከል የ53 ማማዎች ተከላ እና የኤሌክትሪክ ገመድ ዝርጋታ መከናወኑን አቶ አሸናፊ አስታውቀዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ሳይት መሐንዲስ አቶ ሚኒልክ ሠለሞን በበኩላቸው ሻምቡ ከተማ ዳርቻ በዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ የሚገኘው የሻምቡ ባለ 230/33 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር አንድ ባለ 230 ኮሎ ቮልት ገቢ እና ስድስት 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ይኖሩታል ብለዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ግንባታ አራት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እና ሶስት ሚሊዮን ብር የተበጀተለት ሲሆን ከዚህም ውስጥ 85 በመቶው ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር እንዲሁም 15 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ነው፡፡

የቻይናው ሲኖ ሃይድሮ ኩባንያ በዋና ተቋራጭነት፤ ሀገር በቀሉ መላ ኢንጂነሪንግ ደግሞ የሲቪል ሥራውን በንዑስ ተቋራጭነት በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

የጣሊያኑ ኢ.ኤል.ሲ ኤሌክትሮ ኮንሰልታንት ደግሞ የማማከር ሥራውን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አቶ ሚኒልክ አስታውቀዋል፡፡

ከአዲስ አበባ በ335 ኪ.ሜ ርቀት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፤ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን፤ በሻንቡ ከተማ የተገነባው የማከፋፈያ ጣቢያ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለአካባቢው ማህበረሠብ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለ140 ያህል የአካባቢው ነዋሪዎችም ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

4 × 2 =