የስማርት ሜትር ቆጣሪዎችን በራስ አቅም ለመግጠም ታቅዷል

በምዕራብና በሰሜን ሪጅን ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሚተከሉ የስማርት ሜትር ቆጣሪዎችን በራስ አቅም ለመግጠም እቅድ መያዙን በተቋሙ ትራንስሚሻን ሰብስቴሽን ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት የስማርት ሜትር ፕሮጀክት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሃይማኖት ተፈራ አስታወቁ፡፡
በሁሉም ሪጅኖች ከሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች መካከል በ130 ጣቢያዎች ላይ የስማርት ሜትር ቆጣሪ ገጠማ ሥራን ለማከናወን “Siemens Proprietary Limited” ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ስምምነት በማድረግ ስራው ሲከናወን እንደነበር ሥራ አሰኪያጇ አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጅ በሁለቱ ሪጅኖች ላይ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሥራ ተቋራጩ የገጠማ ሥራውን ማከናወን ባለመቻሉ በሪጅኖች የሚተከሉ የቆጣሪ ገጠማ ሥራዎችን በተቋሙ የራስ አቅም ለማከነወን እቅድ ተይዟል ነው ያሉት ኃላፊዋ፡፡
ይህ ሥራ በራስ አቅም እንዲከናወን በተቋሙ ከፍተኛ አመራር በኩል ውሳኔ እንደተሰጠበትም ወ/ሮ ሃይማኖት ተናግረዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ ሃይማኖት ገለጻ በሁለቱ ሪጅኖች በሚገኙ 21 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ 216 የስማርት ሜትር ቆጣሪዎችን ለመግጠም እቅድ ተይዟል፡፡
ለዚህም ስራውን በተገቢው የኮንትራት አስተዳደር መርህ መሰረት ለማከናወን ከስራ ተቋራጩ ለይ በመውሰድ (de-scope በማድረግ) በተቋሙ የራስ አቅም ለመስራት ባለሞያዎችን የማብቃት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
ቆጣሪ የመግጠማ ሥራውን ለማከናወን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የጠቆሙት ወ/ሮ ሃይማኖት በአካባቢዎች የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር መፍትሄ እንዳገኘ ወደ ስራ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
በራስ አቅም ለሚከናወነው ስራም ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ እና 43 ሺህ 1 መቶ የአሜሪካ ዶላር ገንዘብ ከውሉ ላይ ተቀናሽ በማድረግ ለዚህ ስራ በጀት መያዝኑ ነው ስራ አስኪያጇ የተናገሩት፡፡
ስራ ተቋራጩ በ109 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ 9 መቶ 92 የስማርት ሜትር ቆጣሪዎችን መግጠም መቻሉን ወ/ሮ ሃይማኖት ገልፀዋል፡፡
አጠቃላይ የገጠማ ስራውን እስከ ታህሳስ 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን የኮሮና ቫይረስ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተስተዋላው የጸጥታ ችግር፣ የሳይቶቸ በመላው ሀገሪቱ ክፍል ተበታትነው መገኘታቸው እንዲሁም በጉምሩክ በኩል አዳዲስ አሰራሮች በየጊዜው መቀያየራቸው በመርሃ ግብሩ መሰረት ላለመከናወኑ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
የቆጣሪ ገጠማ አጠቃላይ ስራውን (Supply, Installation, Test and Commissioning) ለማከናወን በአለም ባንክ የሚሸፈን ከ25 ነጥብ 28 ሚሊዮን በላይ ብር እና ከ2.17 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር በጀት መያዙን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡
0 Comments