የሴቶችን ተጠቃሚነትና ውሳኔ ሰጭነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ውሳኔዎች ተላልፈዋል

Published by corporate communication on

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሴት ሠራተኞችን ተጠቃሚነትና ውሳኔ ሰጭነትን ለማሳደግ የሚያግዙ የተለያዩ አወንታዊ የድጋፍ እርምጃ (Affirmative action) ዉሳኔዎች መተላለፋቸውን በተቋሙ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢዲኤ እንደገለፁት የተላለፉት ውሳኔዎች የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ውሳኔ ሰጪነትን ለማሳደግና እኩልነትን በተግባር ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ 

ውሳኔዎች የተላለፉት በተቋሙ ሥራ አመራር እና መሰረታዊ ሠራተኛ ማህበር በተመሰረተ ኮሚቴ አማካይነት ጥናትና ውይይቶች ከተካሄዱ በኋላ ነው፡፡

በድርጅቱ ውስጥ የሴቶች የትምህርት ደረጃን ለማሻሻል ለመማር ፍላጎት ያላቸውን ሴት ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች ነፃ የትምህርት እድል የሚያገኙበት ውሳኔ መተላለፉን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ መሰረት በተቋሙ በጀት ተይዞ በየዓመቱ እስከ ዲፕሎማ የትምህርት ደረጃ 25 ሴቶችን፣ በመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት መስክ 20 ሴቶችን እና በሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ደረጃ 10 ሴቶችን ለማሰልጠን የሰው ኃይል እና የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በጋራ በሚያወጡት ግልፅ መስፈርት ተወዳድረው እንዲማሩ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል – ዳይሬክተሯ፡፡

ወ/ሮ ሌንሴ እንደገለጹት ተቋሙ የሴቶችን ፍትሐዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አዲስ ቅጥር በሚያከናውንበት ጊዜ ለፈተና ከሚመረጡ ተወዳዳሪዎች መካከል 30 በመቶው ለሴቶች ዕድል እንዲሰጥና ፈተናውን ካለፉት ተወዳዳሪዎች መካከልም 30 በመቶ ድርሻ ለሴቶች ብቻ እንዲሰጥ ተደርጎ 70 ከመቶ ከወንዶች ጋር ዕድል እንዲሰጥ የሚያደርግ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

በምልመላ ወቅትም ለቦታው መቶ ፐርሰንት የሚያሟሉ አመልካቾች ካልተገኙ 45 በመቶ የአገልግሎት ዘመን የሚያሟሉት ሴት አመልካቾች ተወዳድረው ሊመድቡ የሚችሉበት አሰራርም ተዘርግቷል፡፡

በተቋሙ በየደረጃው የሚገኙ ሴት የስራ መሪዎችን የውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማሳደግ በስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 12.2 መሰረት ለሴቶች በአመራር የስራ መደብ ውድድር ላይ የሚሰጠው 3 ነጥብ የድጋፍ እርምጃ ወደ 10 ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡

ውሳኔው ጊዜያዊ እርምጃ በመሆኑ በድርጅቱ ያለው ፕሮፌሽናል የሆኑ ሴቶች ቁጥር እና የሴቶች ተጠቃሚነትና ውሳኔ ሰጪነት የሚፈለገው ደረጃ ሲደርስ በመመሪያው ላይ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችል ከስምምነት መደረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ውሳኔዎቹ በተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፀድቀው ከታህሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረጋቸውን ከሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

5 × 4 =