የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አበክሮ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ሴቶችን ተሳትፎና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የተቋሙ የሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኤዲኤ ገለፁ፡፡
በተቋሙ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች፣ በኦፕሬሽንና በሁሉም የስራ መስኮች ከጥናት ጀምሮ እስከ ትግበራ ድረስ ባለው ሰንሰለት ሴቶችን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች በስፋት መከናወን እንዳለባቸው በስርዓተ ፆታና ስርፀት ላይ ትኩረት ባደረገው የአምስት ቀናት ስልጠና መዝጊያ ላይ ገልፀዋል፡፡
ወ/ሮ ሌንሴ እንዳሉት ከህብረተሠቡ 50 በመቶ የሚሆኑትን ሴቶች ያገለለ ልማት ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡
በመሆኑም ውጤታማ ስራ ለማከናወን ከተፈለገ ሴቶችን በየደረጃው ተሳታፊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ለአምስት ቀናት በቆየው ስልጠና የስርዓተ ፆታ ምንነትና የተዛቡ አመለካከቶች፣ የስርዓተ ፆታ ትንተና፣ የስርዓተ ፆታ ዓለማቀፋዊና ሀገራዊ ነባራዊ እንዲሁም የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ስትራቲጂካዊ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጧል፡፡
ስልጠናው የተሰጠው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከተለያዩ የስራ ክፍሎች ለተውጣጡ 25 ባለሙያዎች ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ካሉት አጠቃላይ ሠራተኞች ብዛት 15 በመቶዎች ሴቶች መሆናቸውን የተቋሙ የሰው ሀብት መረጃ ያመላክታል፡፡
0 Comments