የሲግናል ርፒተር ጣቢያዎች መገንባት የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቱን ለማዘመን ድርሻቸው የጎላ ነው፡፡

በኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ ለተዘረጋው የኦ.ፒ.ጂ.ደብሊው ፋይበር የመረጃ ልውውጥ ፍሰት መጠናከር እገዛ ያደርጋሉ የተባሉ ሁለት የሲግናል ርፒተር ጣቢያዎች መገንባታቸውን ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ አስታወቀ፡፡
የፕሮጀክቱ ሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ አያሌው እንዳስታወቁት የጣቢያዎቹ መገንባት የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቱን ለማዘመን በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የጎላ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነቡት እነዚሁ ጣቢያዎች በፋይበር መስመሩ የሚደረጉ ማናቸውንም የመረጃ ልውውጦች በጥራት እና በፍጥነት ለማድረስ ያግዛሉ ተብሏል፡፡
እንደ ኢትዮ-ኬንያ ባሉ ረጅም ርቀት ለሚጓዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች የጣቢያዎቹ መገንባት አስተዋጿቸው ከፍተኛ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ በሁለቱ ሃገራት መካከል የሚኖረውን የኮሙዩኒኬሽን ትስስርም አንድ ምዕራፍ ያሻግራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
ጣቢያዎቹ በኮንሶ እና ሜጋ ከተሞች ተገንብተው የተጠናቀቁ ቢሆንም በአንዳንድ ቦታዎች የፋይበር መስመሩ ላይ የስርቆት ወንጀል በመፈፀሙ ምክንያት መስመሩን መልሶ የመጠገን ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በቅርቡም የፍተሻ ሥራ ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ በኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያዎች ላይ ተዘርግተው አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮች ኪራይ በየዓመቱ ተጨማሪ ገቢዎችን እያገኘ ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ የኢትዮ-ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከኃይል ሽያጭ እና ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ የተቋሙን ዓመታዊ ገቢ ያሳድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል::
0 Comments