የሱዳን ኤሌክትሪክ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች አዲስ አበባ ገቡ

Published by corporate communication on

በሱዳን ኤሌክትሪክ ኩባንያ (ሱዳን ኤሌክትሪክ ትራንስሚሽን ኮርፖሬሽን) ዋና ሥራ አስፈጻሚ የቴክኒክ አማካሪ የተመራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል በቀጣይ ስለሚኖረው የኃይል ትስስር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለመደራደር  አዲስ አበባ ገብቷል፡፡

በዋና ሥራ አስፈጻሚው የቴክኒክ አማካሪ ሚስተር አህመድ አደም ኡመር የተመራዉና አምስት አባላትን ያካተተው የልዑካን ቡድን ትላንት ምሽት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስትራቴጂና ኢንቨስትመንት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ተሾመ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

አቶ ወንድወሰን የልዑካን ቡድኑን በተቀበሉበት ወቅት እንደተናገሩት የልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ የገባው በሁለቱ ሃገራት መካከል የኃይል ትስስሩን ለማጠናከር እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ላይ ድርድር ለማድረግ ነው፡፡

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በመገኘት ከኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ድርድር መካሄዱን አስታውሰዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚካሄደው ድርድር ከዚህ በፊት በነበሩ ድርድሮች የተነሱ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙና በቀጣይ ስለሚኖረው የአሰራር ሁኔታ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው ብለዋል፡፡

ድርድሩ የሱዳን የኤሌክትሪክ ኩባንያ ከኢትዮጵያ ተጨማሪ 1 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ባቀረበው ጥያቄ ላይ እንዲሁም  ተጨማሪ ኃይል ለማቅረብ መከናወን ባለበት የመስመር ዝርጋታ እና ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታዎች ላይ ትኩረት የሚያደርግ እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

ድርድሩ ከጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣዮቹ አምስት ቀናት የሚካሄድ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሱዳን 230 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ላይ ትገኛለች፡፡ ከሱዳን በተጨማሪም ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ላይ የምትገኝ ሲሆን  ለኬንያ የአሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ እቅድ መያዙ ተጠቁሟል።

በቀጣይ ከሶማሌ ላንድ፣ ከሶማሊያ፣ ከታንዛኒያ፣ ከኤርትራ፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ለመፍጠር የሁለትዮሽ ግንኙነት በማድረግ ላይ የምትገኝ መሆኑን ከዚህ በፊት በተለያየ ጊዜ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

4 × three =