የሰሜን ምስራቅ አካባቢ የኦፕቲካል ፋይበር መስመሮች ጥገና ተጠናቀቀ

Published by corporate communication on

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ህወኃት በከፈተው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አጋጥሞ የነበረውን የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች እና የኦፕቲካል ፋይበር ገመዶች የመጠገን ሥራ ተጠናቀቀ፡፡

ከደብረሲና – ሸዋሮቢት – ከሚሴ – ኮምቦልቻ – አቀስታ – ዓለም ከተማ ባለ132 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ፤ ከደብረብርሃን – ኮምቦልቻ – ሠመራ  እና ከኮምቦልቻ – አላማጣ እስከ ቆቦ ድረስ ባለ 230 ኪሎ ቮልት መስመር እንዲሁም ከደብረታቦር እስከ ጋሸና ባለ 230 ኪ.ቮ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር በሚያልፍበት አካባቢ የሚገኙ ከተሞችና መንደሮች ላይ ከህዳር 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተደረገው ጥገና አካባቢዎቹ ኤሌክትሪክ መልሰው እንዲያገኙ መደረጉ ይታወሳል፡፡

በተያያዘም ከደሴ – ወልዲያ የ ባለ66 ኪሎ ቪልት መስመር ጥገና በማካሄድ የወልዲያ እና አካባቢው ከተሞች ኃይል እንዲያገኙ ተደርገዋል፡፡

የመልሶ ጥገና ሥራውን ከተቋሙ ስምንት ሪጅኖች እንዲሁም ከተቋሙ የራስ ኃይል የተውጣጣ የጥገና ቡድን በከፍተኛ ርብርብ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ይሁንና ህብረተሰቡ ለበርካታ ሳምንታት እና ወራት በጭለማ ውስጥ እንዳይቆይ ለማድረግ ሲባል የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ጥገናው በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ለተወሰኑ ሰዓታት ኤሌክትሪክ በማቋረጥ ሲሰራ ቆይቶ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ተጠናቋል፡፡

በቀጣይ መስመሩ አገልግሎት እየሰጠ ችግሮች ቢገጥሙት ችግሮቹን የሰሜን ምስራቅ ሪጅን የጥገና ቢሮ እንዲፈታው እና እንደሚከሰተው ችግር ስፋት ደግሞ እገዛ በሚያስፈልገው ቦታ ላይ ከማዕከል የሚንቀሳቀስ የቴክኒክ ድጋፍ ቡድን እገዛ እንዲያደርግ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በአማራና  አፋር  ክልል የደረሰውን የኤሌክትሪክ መሰረተልማት ለመጠገን ለመለዋወጫ አቅርቦት የወጣውን ወጪ ሳይጨምር ለሥራው ብቻ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

3 × 4 =