የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ 68 በመቶ ደርሷል

Published by corporate communication on

በማሻ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የማሻ – መቱ ባለ 230/33 ኪ.ቮ. የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት አጠቃላይ አፈጻጸም 68 በመቶ መድረሱን የማከፋፈያ ጣቢያው የሳይት ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አቶ ፍቃዱ ሁጤሳ ገለፁ፡፡

መሐንዲሱ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ አንድ አዲስ ባለ 230/33 ኪ. ቮ. ከፍተኛ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እና 161 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው የባለ 230 ኪ. ቮ. የኃይል መስመር ዝርጋታን ያጠቃልላል፡፡

እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ በማከፋፈያ ጣቢያው እስከ አሁን የኤሌክትሮ መካኒካልና የብረታ ብረት ተከላና ለኤሌክትሪክ ገመዶች ቀበራ የሚውል ግንባታ እንዲሁም ሁለት ባለ 31 ነጥብ 5 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር ተከላ ሥራዎች ተጠናቀዋል፡፡

የመቆጣጠሪያ ቤት፣ የሰራተኞች መኖሪያ ቤት፣ የጥበቃ ቤት ግንባታና የፍሳሽ ማስወገጃ ግንባታዎች የማጠናቀቂያ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በቀጣይም የጠጠር ንጣፍ፣ የውስጥ አጥር፣ የሲዊችያርድ ግንባታ እና የኬብል ዝርጋታ ሥራዎች  ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚከናወኑ መሐንዲሱ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የማከፋፈያ ጣቢያው አጠቃላይ አፈጻጸም 68 በመቶ ደርሷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከነባሩ የመቱ ባለ 230/66/33/15 ኪ ቮ. የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተነስቶ አዲስ እስከሚገነባው የማሻ ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ የሚዘረጋው የ75 ኪ.ሜ ባለ 230 ኪ. ቮ. ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሥራ በቅርቡ ለመጀመር የተለያዩ ስራዎች ተጀምረዋል፡፡

የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታው 161 ባለ 230 ኪ.ቮ ኃይል ተሸካሚ ማማ ተከላ እና ሽቦ ዝርጋታ ስራ ይኖረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ  ወ/ሮ የትናየት  ይመር እንደተናገሩት የማከፋፈያ ጣቢያውን እና የመስመር ዝርጋታውን ስራ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ከአለም ባንክ በተገኘ የብድር 301 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡

ሥራውን ለመጨርስ 18 ወራት የተያዘለት ሲሆን ግንባታውን ሲኖ ሃይድሮ ኮርፖሬሽን የተባለው የቻይና ኩባኒያ ሲያከናውን በአማካሪነት ደግሞ ኢ. ኤል. ሲ. ELC የተባለ የጣሊያን ኩባኒያ እየተሳተፉበት ይገኛሉ፡፡

ሶስት ባለ 33 ኪ.ቮ. ወጪ መስመር ያሉት ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለማሻና ለአካባቢው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ከማድረጉ ባሻገር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ኃይል ትስስር በማሳለጥ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ  ይጠበቃል፡፡

ከአዲስ አበባ በ700 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በከፋ ሸካ ዞን ማሻ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የማሻ – መቱ ባለ 230/33 ኪ.ቮ. የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት የተጀመረው ህዳር 2012 ዓ.ም. ነበር፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

two × three =