የህዳሴ- ደዴሳ የማስተላለፊያ መስመርን ለአገልግሎት ዝግጁ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው

Published by corporate communication on

በተጠናቀቀው የህዳሴ- ደዴሳ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተለያየ ምክንያት የተሰበሩትን ኢንሱሌተሮችን በአዲስ የመተካት ስራ ተጀመሯል።

የምዕራብ ሪጅን ትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን ቢሮ ዳይሬክተር  አቶ ቶማስ መለሰ እንደገለፁት ኢንሱሌተሮቹን የመተካት ሥራው የተጀመረው በቅርቡ የቅድመ ኃይል ማመንጨት ሥራ ለሚጀምረው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መስመሩን ዝግጁ ለማድረግ ነው፡፡

ኢንሱሌተር የመቀየር ሥራው ከህዳሴ- ደዴሳ – ሆለታ ድረስ ከተዘረጋው መስመር  መካከል እስከ ደደሳ ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ ባለው በሁለቱም የማስተላለፊያ መስመሮች ( ሎት1  እና ሎት2 ) በተተከሉ ምሶሶዎች ላይ የሚከናወን መሆኑን  ዳይሬክተሩ  ገልፀዋል፡፡

 በመስመሩ ላይ በተካሄደለት የፍተሻ ስራ መሠረት በሁለቱም መስመሮች ላይ ከተተከሉት 1 ሺህ 535 ምሶሶዎች መካከል  በ3 መቶ 12 ምሶሶዎች ላይ የሚገኙ ኢንሱሌተሮችን በሌላ የመቀየር ስራ እንደሚከናወን ኃላፊው ጠቁመዋል።

በቀጣይ ከደደሳ ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ሆለታ ማከፋፈያ ጣቢያ በተዘረጋው ባለ 500 ኪሎ ቮልት ማስተላለፊያ መስመር ላይ የተሰበሩ ኢንሱሌተሮችን በተመሳሳይ የመቀየር  ሥራ እንደሚከናወን ተጠቁማል።

የደደሳ ማከፋፈያ ጣቢያ ስምንት ባለ 33 እና ሁለት ባለ 132 እንዲሁም አንድ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ያሉት ሲሆን ከዚህ ውስጥ በአሁኑ ሠዓት ሁለት ባለ 33 እና አንድ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ለነቀምቴ ከተማ እና አካባቢው ኃይል በማቅረብ ላይ ይገኛል።

የህዳሴ ደደሳ ሆለታ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ቻይና ኤሌክትሪክ ቴክኖሎጅ በተሰኘ ኩባንያ መገንባቱ ይታወሳል።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

five × five =