የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የምናደርገውን ድጋፍ እንቀጥላለን – የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራሮችና ሠራተኞች ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና ፈተና ለመመከት በተለያየ መልኩ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋገጡ፡፡

የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች “ደማችን ለሀገራችን” በሚል መሪ ሀሳብ ነሐሴ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተውጣጡ ህዝባዊ የጸጥታ ኃይሎች የሚውል ደም ለግሰዋል፡፡

አመራርና ሠራተኞቹ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እየተካሄደ ላለው የህልውና ዘመቻ አጋርነታቸውን ለማሳየት ሐምሌ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄዱት ውይይት መነሻነት ከ40 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ሲሆን ተቋሙም 25 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ወስኗል፡፡

በደም ልገሳ ፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የሕወኃት አሸባሪ ቡድን ከውጭ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት ሀገሪቱን ለመበታተን የከፈተውን ጥቃት በጋራ መመከት ይገባል፡፡

የደም ልገሳው መርሃ ግብርም የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሕይወቱን እየሰዋ ለሚገኘው ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተውጣጣው ህዝባዊ የጸጥታ ኃይል ያለንን አጋርነት ለማሳየት የተካሄደ ነው ብለዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደገለፁት የደም ልገሳው በጦርነቱ አደጋ ለሚደርሰባቸው የሠራዊቱ አባላትና ደም ለሚፈልጉ ለሌሎች ዜጎችም የሚውል በመሆኑ ሀገርን ለማዳን ሁሉም ህዝብ ከሠራዊቱና ከህዝባዊ የጸጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን በተለያየ መልኩ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው በተቋሙ የፋይናንስ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደመረ አሰፋ፣ አቶ ልብሰወርቅ አስፋው፣ አቶ መለሰ ፋርስ እና ሌሎች የተቋሙ ሠራተኞችም ለህልውና ዘመቻው በተለያየ መልኩ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

ግንባር ላይ ደሙን እያፈሰሰ ለሚገኝ የሠራዊት አባል ደም መለገስ “ሀገር የማዳን” አንዱ አካል ነው ብለዋል ሠራተኞቹ፡፡

የተካሄደው የደም ልገሳ መርሀ ግብር ለሀገር የሚከፈል ዋጋን መደገፍ ነው ያሉት ሠራተኞቹ

በአሁኑ ሰዓት ሀገሪቱ የገጠማትን የህልውና ፈተና ለመመከት ሁሉም ሰው በሚችለው መንገድ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አንስተዋል፡፡

ሀገር ከሌለ ምንም ነገር የለም ያሉት አመራርና ሠራተኞቹ እየተደረገ ያለው የህልውና ዘመቻ ድጋፍ የሀገር ህልውና ቀጣይነትን የሚወስን በመሆኑ በተለያየ መንገድ የሚደረገው ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ በተመደብንበት ሥራ ላይም በኃላፊነት ስሜት የተሰጠንን ሥራ እንፈጽማለን ብለዋል፡፡

የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እየተዋደቀ ላለ ሠራዊት ደም መለገስ ትንሹ ነገር ነው ያሉት የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች በቀጣይ በተለያየ መልኩ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ኢትዮጵያን ከገጠማት ፈተና ለማዳን ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከሌሎች ህዝባዊ የጸጥታ ኃይሎች ጎን የትም፣ መቼም፣ በምንም እንቆማለን የሚለውን ሀገራዊ ንቅናቄ በመቀበል ለእናት ሀገር ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈ ግንባር ድረስ በመዝመት እስከ ሕይወት መስዋት ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

two + thirteen =