የሀገራችንን ሰላም ለማስጠበቅ ሁላችንም በአንድነት እንቆማለን – የኢ.ኤ.ኃ አመራርና ሠራተኞች

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ በአንድነት መቆም እንዳለበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራሮች እና ሠራተኞች አስታወቁ፡፡

የተቋሙ የሥራ መሪዎች እና ሠራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በዛሬው ዕለት ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የተቋሙ የሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ እንደተናገሩት በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ላይ ከውስጥም ከውጭም የተቃጣውን ፈተና ለመታደግ ሁሉም ዜጋ በአንድነት ሊቆም ይገባል፡፡

የህወኃት አሸባሪ ቡድን በሥልጣን ዘመኑ ሀገሪቱን መቀመቅ አውርዷት እንደነበር ያነሱት አቶ ሙላት ከመንበረ ሥልጣኑ ከተወገደ በኋላም የባንዳነት ስራ በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ አሸባሪ ቡድኑን በጋራ መመከት እንደሚገባም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

የተቋሙ ሠራተኞች በበኩላቸው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ እየተሳተፉ ለሚገኙት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተውጣጡት ህዝባዊ የጸጥታ ኃይሎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

“ሁሉን ነገር ማድረግ የሚቻለው ሀገር ስትኖር ነው” ያሉት ሠራተኞቹ፤ ለእናት ሀገር ኢትዮጵያ ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈ ግንባር ድረስ በመዝመት እስከ ሕይወት መስዋዕት ድረስ በመክፈል አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

በተለያዩ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳዎች በመሳተፍ ለአሸባሪው ቡድን ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኙ አካላትን በማጋለጥ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ሠራተኞች አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን እያሉ የሚዝቱ አካላት ራሳቸው ይፈርሱ ይሆናል እንጅ ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይችሉ ሊገነዘቡ ይገባልም ብለዋል ሠራተኞቹ፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የተቋሙ የሰው ኃይል ስራ አስፈፃሚ አቶ አታላይ አበበ እንደገለፁት ሠራተኛው ለህልውና ዘመቻው ከሚያደርገው ድጋፍ ጎን ለጎን የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ለሀገር አለኝታነቱን ማሳየት አለበት ብለዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

3 × three =