ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሰራ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጂነሪንግ የስራ ክፍል የስራ ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድርግ የአቅም ግንባታ ስራ ፕሮጀክት ቀረጾ ወደ ትግበራ መግባቱን የስራ ዘርፉ ስራ አስፈጻሚ ገለጹ፡፡
ስራ አስፈጻሚው አቶ ውድነህ የማነ እንደ ገለጹት በተቋም ድረጃ የተሰጠውን ተልዕኮ እና የስራ ዘርፉን ከኃይል ሽያጭ በተጨማሪ በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በማድረግ አንድ የገቢ አማራጭ ለማድረግ በተቋም ደረጃ የተያዘውን ስትራቴጂክ እቅድ ለማሳካት ሥር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ የአቅም ግንባታ ስራዎች ፕሮጀክት ቀርጾ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ የብድር ድጋፍ የሚከናወነው ይህን ፕሮጀክት በዘርፉ በርካታ ልምድ ያለው ኤሌክትሮ አማካሪ (ELC Electro-consult) የተባለ የኢጣሊያን ኩባንያ ጋር ውል በመፈራረም ከጥቅምት 16 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ስራ መገባቱን ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡
በሰራ ዘርፉ ያሉት ስድስት ዳሬክተሮች እና ሁለት ማናጀሮች በዋናነት የሚመሩት እና የስራ ዘርፉ ሰራተኞች ተሳታፊ የሚሆኑበት የአቅም ግንባታ ስራው የሚከተሉት አራት ዋና ዋና አላማዎች እንዳሉት አቶ ውድነህ የገለጹ ሲሆን እነርሱም ፡-
1ኛ አሁን ያለውን የክፍሉን አሰራር ስርአትና አወቃቀር አለማቀፍና ተወዳዳሪ ከሆኑ የአማካሪ ድርጅቶች ጋር ንፅፅር በማድረግ ያለውን ክፍተት መለየትና ፤ ክፍተቱን ለመሙላት የሚያስችል ስራዎችን ማለትም የቢዝነስ ፕሮሰስ ዲዛይን፤ ፖሊሲ ፤ ፕሮሲጀር፤ ፎርም፥ ቴምፕሌት ፤ መመሪያና ማኑዋል መዘጋጀት፡፡
2ኛ የክፍሉን ሰራተኞች አቅም ለመጨመር የሚያስችሉ ስልጠናዎች መስጠት ሲሆን፤ በዚህ ረገድ ሁሉንም የስራ ክፍሎች የሚያከናውናቸውን ስራዎች ሊያግዙ የሚችሉ ሰፋ ያሉ ስልጠናዎች ከመስጠት በተጨማሪ ለክፍሉ የሚያስፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በተደራጀና ቀጣይነት ባለው መልኩ ማሰልጠን እንዲቻል የስልጠና ስትራቴጂክ እቅድ ማዘጋጀት፡፡
3ኛ የውሃ ኃይል ማመንጫ፣ የፀሃ ኃይል ማመንጫና፤ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን በተመለከተ የአለማቀፍ አበዳሪዎችና ማዕቀፍ(framework) ታሳቢ ባደረገ መልኩ የቅድመ ጥናትና ዲዛይንሰ ሰራዎችን ለማገዝ የሚያስችሉ የዲዛይንና አናላሲስ ሶፈትዌር ግዢን ማከናወን ፡፡
4ኛ ክፍሉን በቀጣይ በዘርፉ የሚኖረውን ተወዳዳሪነት ለመጨመር የሚያስቸሉ ስራዎችን በማከናወን የክፍሉን የቢዝነስ ሞዴል መቅረፅ ፤ ወደ ማማከር ገበያ ለመግባት የሚያስችል የማርኬቲንግ ስትራቴጂክ እቅድ ማዘጋጀት ፤ እንዲሁም የቢዝነስ ቀጣይነትና አስተማማኝነትን የሚያረጋግጥ እቅድ ማዘጋጀት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የአቅም ግንባታ ስራዎቹን በ14 ወራት ለማጠናቀቅ እቅድ የተያዘለት ይህ ፕሮጀክት የ 1,518,160.00 የአሜሪካ ዶላር እና የ11,215,586.00 የኢትዮጵያ ብር የፋይናስ ወጪ በጀት ተይዞለታል፡፡
ሁሉም የሚመለከታቸው ሰራተኞች ፕሮጀክቱን በንቃት በመሳተፍ በቀጣይ ለሚጠበቅባቸው ትልቅ ኃላፊነት እራሳቸውን ከወዲሁ ማዘጋጀት እንደ ሚጠበቅባቸው ኃለፊው አስገንዝበዋል፡፡
0 Comments