ወቅታዊ እና ጤናማ የሂሳብ ሪፖርት ለማቅረብ እየተሰራ ነው

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያን ኤሌክትሪክ ኃይል ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርት ጤናማ እንዲሆን ለማድረግ እና ወቅታዊ የሂሳብ ሪፖርት ለኦዲት አገልግሎት ቦርድ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የተቋሙ የፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ  አስታወቁ፡፡

ሥራ አስፈፃሚው አቶ ደመረ አሰፋ እንደገለፁት የተቋሙን የ2012 በጀት ዓመት የሂሳብ ሪፖርትን ለኦዲት አገልግሎት ቦርድ በወቅቱ ለማቅረብ እና ሪፖርቱ ጤናማ እንዲሆን ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የሚመረመረውን የተቋሙን የ2012 በጀት ዓመት ሂሳብ ሪፖርት ለኦዲት አገልግሎቱ በወቅቱ ለማቅረብ የሂሳብ መዝጋት ስራ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

የተቋሙ የኦዲት ሪፖርት ከ2009 በጀት ዓመት ጀምሮ ቀደም ሲል ከነበረበት የትችት አስተያየት (disclaimer) ነፃ መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው አስታውሰዋል፡፡

የ2012 በጀት ዓመት ሂሳብን ለኦዲት አገልግሎት በወቅቱ በማቅረብ በ2009 የተሰጠውን የኦዲት አስተያየት ለማስቀጠልና የኦዲት ሪፖርቱ ጤናማ እንዲሆን ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት በመሰራት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

የተቋሙን ሂሳብ እንደ ሀገር በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ ሪፖርት ስርዓት (IFRS) እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደመረ በአሁኑ ወቅትም የተቋሙ ቋሚ ንብረት ቆጠራና የዋጋ ክለሳ ስራ በረቂቅ ደረጃ ተጠናቋል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ደመረ ገለፃ ተቋሙ የፋይናንስ ሪፖርት ስርዓቱን በዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ ስርዓት ሲስተም ለማዘጋጀት የንብረት ዋጋ ክለሳ ሪፖርት እየጠበቀ ነው፡፡

ይህም ጥራትና ታማኝነት ያለው እንዲሁም ተወዳዳሪ የሆነ የፋይናንስ ሪፖርት ለማቅረብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

16 + 6 =