ኮሚቴው የመስክ ምልከታ ጉብኝት አደረገ

Published by corporate communication on

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት ውኃ፣መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ታህሳስ 7 ቀን 2013 ዓ.ም  በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመስክ ምልከታ ጉብኝት አካሄደ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታውን ያደረገው በዋናነት በረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እና በኮተቤ መጋዘን ላይ ያለውን የተቋሙ የንብረት አያያዝ ሥርዓት የተመለከተ ነው፡፡ 

ረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ  ጣቢያ ታቅዶ ከተገነባበት ፍላጎት አንጻር አሁን ላይ ያለበት ደረጃ እና የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን አስተማማኝነት ላይ ዳሰሳ አድርጓል፡፡

የከተማውን ደረቅ ቆሻሻ  ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል በመቀየር ሂደት ውስጥ እስካሁን ያስገኘው ጠቀሜታ እና ከፕሮጀክቱ የሚወጡ ተረፈ ደረቅ ቆሻሻዎች የሚወገዱበት ሥርዓት ከአካባቢ ብክለት ነፃ ስለመሆኑ ኮሚቴው ተመልክቷል፡፡

ተቋሙ የደረቅ ቆሻሻ የሚያሰባስቡ ግለሰቦችና ማህበራት ለጣቢያው ግብዓት የሚሆን ደረቅ ቆሻሻ ለይተው እንዲያቀርቡ የፈጠረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ምን ያህል እንደሆነም ኮሚቴው በጥያቄ አንስቷል፡፡

በተያያዘ ተቋሙ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን መዝግቦ በማስቀመጥ ከብክነት የፀዱ ስለመሆናቸው እና ከአገልግሎት ውጭ የሆኑትን የአወጋገድ ሥርዓት ስለመኖሩ አስተያት እንዲሰጥበት ኮሚቴው አንስቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ሌሎች በተቋሙ ላይ የሚታዩ ከተቋማዊ ሪፎርም፣ ከይዞታ ማረጋገጫ፣ ከኮሮና መከላከያ ፕሮቶኮል እና ከህጻናት ማቆያ ዝግጅት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ማብራሪያ ጠይቋል፡፡

በመስክ ምልከታ ጉብኝቱ መልስ እንዲሰጥባቸው በተነሱ ጉዳዮች ላይ የተቋሙ ማኔጅመንት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

ተቋሙ በኃይል ማምንጫ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሚስተዋለውን የሰው ኃይል፣ የጥገና እና መለዋወጫ አቅርቦት እጥረት በመቅረፍ፣ የሠራተኛው ደህንነት በመጠበቅ እንዲሁም ያለውን ንብረት በአግባቡ ተጠቅሞ ሀገራዊ ሪፎርሙን ለማሳካት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርቷል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

twelve + thirteen =