ክለቡ በውድድር  ዓመቱ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች መካከል የተሸነፈው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው

Published by corporate communication on

ወደ ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተቀላቀለው ኢትዮ- ኤሌክትሪክ በውድድር  ዓመቱ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች መካከል 11 ጨዋታዎችን አሸንፎ፣ በስድስቱ አቻ በመውጣትና በአንድ ጨዋታ ብቻ በመሸነፍ ጠንካራ ተፎካካሪነቱን አሳይቷል፡፡

በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና መሪነት የ2014 ዓ.ም የከፍተኛ ሊግ ውድድሩን የተቀላቀለው አንጋፋው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ከፍተኛ ትንቅንቅ የታየበትን ምድብ ሀ በመምራት 26 ጎሎችን አስቆጥሮ በ39 ነጥብ ሊጉን በመሪነት አጠናቋል፡፡

በ2010 ዓ.ም ከፕሪሚየር ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደው አንጋፋው ክለብ ከ4 የውድድር  ዘመን  በኋላ ዋንጫ በማንሳት ጭምር ያለመውን ማሳካት ችሏል፡፡

በአጠቃላይ በዓመቱ 18 ጨዋታዎችን ያደረገው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ11 ጨዋታዎች አሸንፎ፣ በስድስቱ አቻ ወጥቶ በአንድ ጨዋታ ብቻ ተሸንፎ በ39 ነጥብ ሊጉን በመሪነት አጠናቋል፡፡

አንጋፋው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ምንያህል ተሾመን ጨምሮ እንደ ፀጋ ደርቤ እና ኢብራሂም ከድር ያሉ ተስፈኛ ወጣቶችን አሰባጥሮ ወደ ውድድር የገባው ኢትዮ ኤሌክትሪክ (ኮረንቲ) የተጫዋቾችን የልምድ ሚዛን ጠብቆ በመጓዝ ለድል ሊበቃ ችሏል፡፡

ከሻምፒዮንነቱ ባሻገር  ኮከብ አሰልጣኝ፣ ኮከብ ጎል አግቢ እና ኮከብ ግብ ጠባቂ በማስመረጥ  በውድድር ዓመቱ ድርብርብ ውጤት አስመዝግቦ ታሪካዊ አሻራ ማሳረፍ ችሏል፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለፉት የእግር ኳስ ዘመናት እንደ ፈቃደ ሙለታ፣ ቅጣው ሙሉ፣ ጠንክር አስናቀ፣ ዮርዳኖስ ዓባይ፣ ሲሳይ ተሰማ፣ ኤሊያስ ጁሀር እና አንዋር ሲራጅ ያሉ አይረሴ ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በማበርከት የሀገር አለኝታነቱን ያስመሰከረ የ60 ዓመት ታሪክ ያለው ክለብ ነው፡፡

ክለቡ በተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን ታማኝ ደጋፊዎችን በማፍራት የሚታወቅ ሲሆን ዋንጫውን በተረከበበት ወቅት አሁን በህይወት ለሌሉትና በክለቡ የደጋፊዎች ታሪክ ሁሌም ለማይረሱት ነፍስሔር ሐጂ  ኑር ሁሴን እና ነፍስሔር በቀለ ኮረንቲ  የአንድ ደቂቃ የመታሰቢያ ፀሎት በማድረግ አስቧቸዋል፡፡

የኢትዮ- ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ  የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ማደጉን ተከትሎ ትናንት ምሽት በስካይ ላይት ሆቴል ለተጫዋቾቹና ለክለቡ አባላት ዕውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

2 + 13 =