ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የቢሾፍቱ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ

ከአዲስ አበባ በ45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በቢሾፍቱ ከተማ የተገነባው ባለ 400/230/15 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሄር ገለጹ፡፡
አቶ ዳዊት እንደገለፁት የማከፋፈያ ጣቢያው የግንባታ፣ የፍተሻ እና የሙከራ ስራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡
ከነባሩ አቃቂ – ገላን ባለ 400/230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ተነስቶ እስከ ቢሾፍቱ ማከፋፈያ ድረስ 46 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ጥንድ ባለ 400 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታም ተከናውኗል፡፡
የፕሮጀከቱ የሳይት ተቆጣጣሪ መሃንዲስ አቶ ዘውዱ ለገሰ እንደገለፁት ማከፋፈያ ጣቢያ ሁለት ባለ 600 ሜጋ ቮልት አምፒር እና ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ትንስፎርመሮች ተተክለውለታል፡፡
ጣቢያው ጥንድ ባለ 400 ኪሎ ቮልት ገቢ መስመር እና ሁለት ጥንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት እንዲሁም 10 ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት፡፡
የማከፋፋያ ጣቢያውን የገነባው ላርሰን ኤንድ ቱቡሮ የተባለ የህንድ ኩባንያ ሲሆን ግንባታው ለመጨረስ ከ25 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያው መገንባት በቢሾፍቱ ከተማ እና በዙሪዋ ለሚገኙ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችና የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ለህብረተሰቡ የኃይል ፍላጎት ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይታመናል፡፡
0 Comments