ከ1 ሺህ 3 መቶ ኪ.ሜ በላይ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና 14 የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

በ2013 በጀት ዓመት የ1 ሺህ 304 ነጥብ 2 ኪ.ሜ የማስተላለፊያ መስመርና 14 የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ፕሮግራም መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ኃላፊ ወ/ሮ ጽዮን ብርሃኑ እንዳስታወቁት በአሁኑ ሰዓት በመላው ሀገሪቱ የተለያየ የኪሎ ቮልት መጠን ያላቸው 14 የማስተላለፊያ መስመር እና 34 የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በግንባታ ላይ ከሚገኙት የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክቶች መካከል 433 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር ባለ 500 ኪ.ቮ፣ 1045 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ባለ 400 ኪ.ቮ፣ 949 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ባለ 230 ኪ.ቮ እና 191 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ባለ 132 ኪ.ቮ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡
የሚገነቡት የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ደግሞ አንድ ባለ 500 ኪ.ቮ፣ አምስት ባለ 400 ኪ.ቮ፣15 ባለ 230 ኪ.ቮ እና 13ቱ ማከፋፈያ ጣቢያ ባለ 132 ኪ.ቮ ናቸው፡፡
በግንባታ ላይ ከሚገኙት ፕሮጀክቶች መካከል አራቱ በራስ ኃይል በመከናወን ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ወ/ሮ ጽዮን ገልጸዋል፡፡
በግንባታ ላይ ካሉት የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች መካከልም የ14 ማከፋፈያ ጣቢያ እና የ1 ሺህ 304 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ግንባትን በ2013 በጀት ዓመት በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለማስገባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በግንባታ ላይ ከሚገኙት ፕሮጀክቶች መካከል አራቱ በራስ ኃይል በመከናወን ላይ የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡
ከአዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተጨማሪ በአንዳንድ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ አቅም የማሳደግ ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ነው ወ/ሮ ጽዮን የተናገሩት፡፡
እንደ ወ/ሮ ጽዮን ገለፃ የፕሮጀክቶችን ግንባታ በተያዘላቸው መርሃ ግብር ለማከናወን የወሰን ማስከበር ችግር፣ የፀጥታ ሁኔታ፣ የግብኣት አቅርቦት ችግር፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ መደረጉ፤ የሙከራና ፍተሻ ስራ በወቅቱ አለመከናወኑ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡
በአሁኑ ሰዓት በግንባታ ላይ የሚገኙት የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ለ2 ሺህ 661 ያህል ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ችለዋል፡፡
በተያዘው የበጀት ዓመት በአማራ፣ በደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች አምስት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚጀመርና የአራት ማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም የማሳደግ ስራ እንደሚሰራ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
በ2013 በጀት ዓመቱ የታቀዱ ስራዎችን በመርሃ ግብራቸው ለማከናወን የካሳ ክፍያ ጥያቄ፣ የፀጥታ ሁኔታ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ኮሮና ቫይረስ እና ከታክስ ጋር በተገናኘ ከዕቃ ማጓጓዝ ላይ የተጫነው የታክስ አዋጅ እንደ ስጋት የተለዩ ችግሮች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በመምሪያው ከሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በተቋሙ የራስ ኃይል ቢሮ በርካታ የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ከ18 ሺህ 8መቶ ኪሎ ሜትር በላይ የማስተላለፊያ መስመርና ከ2 መቶ በላይ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
0 Comments