ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች የኃይል መሰረተ ልማት በራሳቸው በጀት ሊያሟሉ ይገባል

ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች የኃይል ፍላጎት ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ የኃይል መሰረተ ልማት አሟልተው ወይም ለመሰረተ ልማት ዝርጋታው የሚያስፈልገውን ፋይናንስ አቅርበው ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ተቋሙ በተሻሻለው ደንብ ቁጥር 381/2008 መሰረት በዋናነት ከብሔራዊ የኃይል ቋት (National Grid) ጋር የተገኛኙ ማመንጫዎችን፣ ከ66 ኪሎ ቮልት በላይ የሆኑ ማከፋፋያ ጣቢያዎችንና የኃይል ተሸካሚ መስመሮችን የመገንባት፣ የማስተዳደርና የዲዛይን ስራዎችን እንዲሰራ ተልዕኮ ተሰጥቶታል፡፡
ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚዎች ኃይል በጅምላ የሚያቀርብና የሚሸጥ ቢሆንም የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ስኳር ፋብሪካዎች፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና ሌሎች ድርጅቶች ኃይል ለማግኘት ሲፈልጉ የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታዎችን አስቀድመው በማሟላት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ሞገስ ገለፃ ለተጠቃሚው ቅርብ የሆነ መስመር ወይም ማከፋፈያ ጣቢያ ከተለየ በኋላ እስከተጠቃሚው የሚደርሰው የኃይል መሰረተ ልማት ወጪ የሚሸፈነው በኃይል ጠያቂው በመሆኑ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ጥያቄ ጋር ሆኖ ለተቋሙ እየቀረበ ነው፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመንግስትም ሆነ በግል ባለሀብቶች ለሚሰሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ኃይል ማቅረብ እንጂ የኃይል መሰረተ ልማት የመዘርጋት ኃላፊነት እንደሌለበት ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡
በመገንባት ላይ ያሉና ወደ ፊት የሚገነቡ ከፍተኛ ኃይል የሚፈልጉ ፕሮጀክቶችም ይህን በመገንዘብ የሚፈልጉትን የኃይል መሰረተ ልማት ዝርጋታ የፕሮጀክታቸው አካል በማድረግ ሊሰሩ እንደሚገባ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
የአዋሽ – ወልዲያ – ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ጉዳይም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ በመግለጫቸው አብራርተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለባቡር ፕሮጀክቱ ብቻ የሚውለውን (dedicate line) የኃይል መሰረተ ልማት ዝርጋታ ሳያከናውን ኃይል አልተለቀቀልኝም በሚል በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጀመረውን ዘመቻ ህግን ያልተከተለ እና ህብረተሰቡን የሚያሳስት በመሆኑ ከድርጊቱ ሊታቀብ ይገባል፡፡
ለባቡር ፕሮጀክቱ የሚሆነውን መሰረተ ልማት በራሱ እንዲዘረጋ አልያም በጀት አፈላልጎ እንዲያሰራ በተደጋጋሚ በኃላፊዎች ደረጃ በተደረጉ ውይይቶችና በደብዳቤ ተቋማችን ቢያሳውቀውም ኮርፖሬሽኑ ኃላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉ ፕሮጀክቱ መዘግየቱን ጠቅሰዋል፡፡
ይሁንና ለባቡር ፕሮጀክቱ ብቻ የሚውለውን የኃይል መሰረተልማት ግንባታ በማጠናቀቅ የኃይል አቅርቦቱን ማግኘት እንደሚችል ተብራርቷል፡፡
ለፕሮጀክቱ ፋይናንስ ከማፈላለግ ጀምሮ አማራጮችን በማመላከት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኮርፖሬሽኑ ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት ዳይሬክተሩ አሁንም ከፋይንስ ውጪ የሆኑ ድጋፎችን ለመስጠት ተቋሙ ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል፡፡
0 Comments