ከፀሀይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

Published by corporate communication on

በአፋር እና ሱማሌ ክልል ከፀሀይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል፡

ስምምነቱን አስመልክቶ ታህሳስ 9/2012 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠ ሲሆን የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የአክዋ ፓወር ኩባንያ ኃላፊዎች መፈራረማቸውን ተገልጿል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ተሾመ ታፈሠ (ዶ/ር) ሁለቱ የፀሀይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በሱማሌ ብሔራዊ ክልል ልዩ ስሙ ጋድ እንዲሁም በአፋር ብሔራዊ ክልል ዲቾቶ በተባሉ ቦታዎች ላይ እንደሚገነቡ አስታውቀዋል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች እያንዳንዳቸው 125 ሜጋ ዋት በድምሩ 250 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዲኤታው ግንባታቸውን ለማከናወንም 300 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ በኃይል ልማቱ ዘርፍ የግል ባለሃብቱንና ኩባንያዎችን በማሳተፍ፤ የኃይል ዘርፉን በማዘመን ብሎም የመንግስትን የዕዳ ጫና በማቃለል ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የገለፁት ዶክተር ተሾመ አጠቃላይ የጨረታ ሂደቱም ዓለም ዓቀፍ መስፈርትን የተከተለ ነው ብለዋል፡፡

በፋይናንስ ሚኒስቴር የመንግስት እና የግል አጋርነት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጥላሁን ታደሠ በስምምነቱ መሠረት የፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምሩ የሳውዲ ዓረቢያ ኩባንያ የሆነው የአክዋ ፓወር ኩባንያ አንድ ኪሎ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይልን በ 2.526 የአሜሪካን ሳንቲም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚሸጥና ይህም ከዓለም አቀፍም ሆነ ከአፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ተመን ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛ ዋጋ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኃይል ማመንጫዎችን አክዋ ፓወር ኩባንያ ለ20 ዓመታት እንደሚያስተዳድርም ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጂነሪንግ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዷለም ሲዓ በበኩላቸው የጋድ የፀሀይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በ18 ወራት የዴቻቶን ደግሞ በ15 ወራት ለማጠናቀቅ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከውሃ 50 ሺህ ሜጋ ዋት፣ከንፋስ እስከ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት፣ ከምድር እንፋሎት (ጂኦተርማል) 10 ሺህ ሜጋ ዋት እና ከፀሀይ ኃይልም ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላት መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

thirteen + 11 =