ከግድቡ የሚለቀቀዉ ዉሃ ድንገተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ እንዳይከሰት ለመቆጣጠር ያግዛል

የጊቤ 3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግድብ እየሞላ በመምጣቱ ውሃ በየደረጃው ለመልቀቅ የሚያስችል የሙከራ ስራ ተከናውኗል፡፡
ከግድቡ የሚለቀቀው ዉሃ ወደፊት በታችኛው ተፋስስ ላይ ጎርፍ እንዳይከሰት ለመቆጣጠር እና ውሃውን በተመጠነ መልኩ በመልቀቅ በክረምቱ መጨረሻ ላይ ግድቡ ሙሉ እንዲሆን ለማድረግ በማስፈለጉ እንደሆነ የጣቢያው ስራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ ሰሙ ገልፀዋል፡፡
ውሃ ከግድቡ በየደረጃው እንዲለቀቅ መደረጉ በተፋሰሱ ውስጥ የጎርፍ መቆጣጠር ስራ ለማከናወን እንደሚያግዝም ጠቁመዋል፡፡
ግድብ የመጣውን ጎርፍ ሁሉ እንደመጣ ላለመልቀቅና የተመጠነ የውሃ ፍሰት እንዲኖር ለማድረግም በየጊዜው እየተቆጣጠሩ መልቀቅ ክረምቱ ሲጠነክር ሊከሰት የሚችለውን ጎርፍ ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ሃብታሙ ገለፃ ግድቡ መያዝ ከሚችለው 15 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ውስጥ 12 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ የያዘ ሲሆን በሴኮንድ በአማካኝ 800 ሜትር ኪዩብ ውሃ ለመልቀቅ እቅድ ተይዟል፡፡
ግድቡ ባለፈው ዓመት ህዳር ወር ከባህር ጠለል በላይ 882 ሜትር ላይ በመድረስ ከፍተኛ ውሃ መያዝ የቻለ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ከዚህ መጠን ጋር ተመሳሳይ ውሃ መያዙን ተናግረዋል፡፡
ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከሦስት ወር አስቀድሞ ከባህር ጠለል በላይ 892 ሜትር ላይ በመድረስ ሊሞላ እንደሚችል ያመለክታል፡፡
ውሃው ከአሁኑ ካልተለቀቀ ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ሙሉ በሙሉ ሊሞላ እንደሚችልም ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
ግድቡ አሁን ሳይለቀቅ ቆይቶ ከሞላ በኋላ የሚለቀቅ ከሆነ ከላይኛው የጊቤ ተፋሰስ የሚመጣውን ጎርፍ ሁሉ ለመልቀቅ ስለሚያስገድድ በታችኛው ተፋሰስ ላይ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡
ይሁንና የግድቡ ውሃ በየቀኑ እየጨመረ ስለሚሄድ ውሃ የመልቀቅ ሂደቱን ቀስ በቀስ መጥኖ በማከናወን ከግድቡ በታችኛው ተፋሰስ በሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ አደጋ እንዳያስከትል እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ውሃ ሲለቅ የመጀመሪያው ሲሆን የውሃ መልቀቅ ሂደቱ እስከመቼ ሊቆይ እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም፡፡
0 Comments