ከጀርመን መንግስት የተወጣጡ ልዑካን የረጲ ደረቅ ቆሻሻን ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ጎብኙ

ከጀርመን መንግስት ፓርላማ አባላት እና ባለሃብቶች የተወጣጡ የልዑካን ቡድን አባላት የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ጎብኙ፡፡
የልዑካን ቡድኑን የተቀበሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዳርጌ እሸቴ ናቸው፡፡
ሥራ አስፈጻሚው እንደገለፁት ጣቢያው የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት በተጨማሪ ከበካይ ጋዝ ነጻ የሆነ የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት ለመፍጠርና የከተማውን ጽዳት እና ውበት ለመጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
የልዑካን ቡድኑ መሪ የሆኑት በጀርመን መንግስት የባድንቩትምበርግ ኢንቫሮመንት ቴክኒክ ኢንስቲትዩት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኢንጂነር ሃንስ ሺፒት በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት ጀርመን በተመሳሳይ የኃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂ በርካታ ልምድ እና ኩባንያዎች ያሏት በመሆኑ በቀጣይ በዘርፉ ያላቸውን ልምድ ለማጋራት እና ለመደገፍ በትብብር እንሰራለን ብለዋል፡፡
ረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች መካከል ይገኛል፡፡
ኃይል ማመንጫው ሁለት የእንፋሎት ተርባይኖች እና ጄኔሬተሮች ሲኖሩት በዓመት 185 ጌጋ ዋት ሰዓት (185GWh) ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡
ጣቢያው ኃይል ማመንጨት ከጀመረበት ከሚያዚያ 4 ቀን 2011ዓ.ም. ጀምሮ አስከ ህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ 262 ቶን ቆሻሻ በማቃጠል 107 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክተሪክ ኃይል ማመንጨቱን የጣቢያው የኤሌክትሪካል መሃዲስ አቶ አስተዋይ ጎንፋ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል (ኢ.ኤ.ኃ) በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ደረቅ ቆሻሻን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይልነት መቀየሩ የተመሰከረለትን ቴክኖሎጂ በሀገሪቱ ውስጥ ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡
ረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች መካከል የሚገኝ ሲሆን የ3ኪሎ ሜትር ባለ 132ኪ.ቮ. ከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር አለው፡፡
ጣቢያው ከባህር ጠለል በላይ በ 2275 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡
ረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራው በይፋ የተጀመረበት ቀን መስከረም 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲሆን ነሃሴ 2010 ዓ.ም. በይፋ ተመርቆ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ይህ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከመዲናዋ በየቀኑ የሚሰበሰበውን 1400 ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻ የሚያቃጥል በመሆኑ የከተማዋን የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት በማዘመንና ውበቷን በመጠበቅ በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጠ የሚገኝ ነው፡፡
0 Comments