ከተቋሙ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ውስጥ 33 ነጥብ 1 በመቶዎቹ በራስ አቅም የተገነቡ ናቸው

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችንና የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶችን በራስ ኃይል የመገንባት አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን የሲቪል ስራዎች ቢሮ ገለፀ፡፡

የቢሮው ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ኃይለ ጊዮርጊስ እንደገለፁት ተቋሙ ከባለ 45 ኪሎ ቮልት ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን በራስ ኃይል መገንባት የጀመረው ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ ነበር፡፡

ቢሮው በሰው ኃይልና በመሳሪያ ተደራጅቶ በአሁኑ ሰዓት እስከ 400 ኪሎ ቮልት ድረስ ያሉ የማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አቶ ሰሎሞን ተናግረዋል::

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙት የከፍተኛ መስመሮች ውስጥ 30 ነጥብ 3 በመቶው እንዲሁም ከኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ውስጥ 33 ነጥብ 1 በመቶዎቹ በራስ ኃይል ቢሮ የተገነቡ መሆናቸውን አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ሰሎሞን ገለፃ ቢሮው ከአዳዲስ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በ59 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የማስፋፊያ እና በ37 ማከፋፈያ ጣቢያዎች አቅም የማሳደግ ስራ አከናውኗል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ተቋሙ ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆን ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ፣ የአዳዲስ ማከፋፈያ ጣቢያዎችንና በነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የማስፋፊያ ስራዎችን እንዲሁም የሌሎች ፕሮጀክቶችን የግንባታ ስራ በራስ ኃይል በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በራስ ኃይል የፕሮጀክቶችን የግንባታ ስራ ማከናወኑ ለሀገሪቱ የዉጪ ምንዛሪ ወጪን ከማስቀረት በተጨማሪ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ዜጎች ሀገራዊ ስሜት እንዲሰማቸዉ ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት፡፡

አቶ ሰለሞን እንዳሉት ፕሮጀክቶች በራስ ሃይል እንዲከናወኑ መደረጉ ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ ለማከናወን እና በመርሃ ግብራቸው መሰረት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

9 − three =