ከሠራተኛው ጎን መቆም ግዴታችን ነው – አቶ አሸብር ባልቻ

ችግሮችን ለመፍታት ከሰራተኛው ጎን መቆም መልካም ፈቃድ ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ጭምር ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ ተናገሩ፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው በተጠናቀቀው የተቋሙ መሰረታዊ የሠራተኛ ማህበር 7ኛ የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጉባኤ ላይ እንደገለፁት ተቋሙ በ2013 በጀት ዓመት ከሠራተኛ ማህበር ጋር በመሆን የሠራተኛውን ችግሮች በመፍታት እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሠራተኞች ለመድረስ በሚቻለው አቅም ተንቀሳቅሷል፡፡ ይህንንም በቀጣይ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተካሄደው የህግ ማስከበር ሥራ በሰሜን ሪጅን ለሚገኙ ሠራተኞች ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ እንዲሰጥ መደረጉ እና በአዋሽ 2 እና 3 ኃይል ማመንጫ በድንገተኛ የእሳት አደጋ ቤት ንብረት ለወደመባቸው 19 የኃይል ማማንጫው ሠራተኞች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ንብረታቸው እንዲተካለቸው መደረጉን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠቅሰዋል፡፡
ማንኛውም የተቋሙ ሠራተኛ በሞት በሚለይበት ወቅት የሁለት ወር ደመወዝ ተሰልቶ ለሟች ቤተሰብ ወይም ለህጋዊ ወራሽ ለቀብር ማስፈጸሚያ እንዲሰጥ የሚያደርግ አሰራር ተዘርግቶ ከሚያዚያ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ እንዲሚገኝ አቶ አሸብር ጠቁመዋል፡፡
የተቋሙን ሠራተኞች ውጤታማ ለማድረግ ማኔጅመቱም ሆነ ቦርዱ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ ያሉት ሥራ አስፈፃሚው የሠራተኞችን ችግሮችን ለመፍታት ከሰራተኛው ጎን መቆም መልካም ፈቃድ ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ጭምር ነው ብለዋል ፡፡
ከአዋሽ ኃይል ማመንጫ የተገኙት የዘርፍ ማህበር ተወካይ አቶ ምናለ ወልዴ ለተቋሙ አመራሮች ቦታው ድረስ በመላለስ ተጎጂዎችን እና እንዲጽናኑ እና ደግፍ እንዲያገኙ በማድረግ ለሠራተኛው አለኝታነታቸውን በተግባር በማረጋገጣቸው በሠራተኛው ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
0 Comments