ከሀገር ውስጥ የኃይል ሽያጭ እና ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል

Published by corporate communication on

በተያዘው የ2013 በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ የኃይል ሽያጭ እና ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን የማርኬቲንግና ቢዝነስ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት 12 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት(12 ሺህ 900 ጊጋ ዋት ሰዓት) የኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች በማቅረብ 8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል፡፡

ከመምሪያው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ገቢው የሚሰበሰበው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በጅምላ ከሚቀርብ የኃይል ሽያጭ፣ ከከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከሚጠቀምበት የፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ እና ከኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር የኃይል አቅርቦት ነው፡፡

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ካቀደው ውስጥ 89 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብሩ ኢትዮ ቴሌኮም ከሚጠቀምበት 8,443 ኪሎ ሜትር የፋይበር ኦፕቲክስ (OPGW) ኪራይ፣ 7 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብሩ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሚቀርብ የጅምላ ኃይል ሽያጭ፣ 987 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብሩ ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንደስትሪዎች እንዲሁም 47 ነጥብ 88 ሚሊዮን ብሩ ለኢትዮ- ጅቡቲ ምድር ባቡር ከሚቀርበው የኃይል ሽያጭ ለመሰብሰብ የታቀደ ነው፡፡

ተቋሙ በ2013 በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ ኃይል ሽያጭና ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ ለመሰብሰብ የያዘው እቅድ ከ2012 በጀት ዓመት ዕቅድ ጋር ሲነፃፀር ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ተቋሙ በ2012 በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ የኃይል ሽያጭ እና ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ ከ6 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ በመሰብሰብ የእቅዱን 102 ነጥብ 2 በመቶ ማሳካት እንደቻለ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የተቋሙ ዓመታዊ ገቢ በ2006 በጀት ዓመት ከነበረበት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በየዓመቱ እያደገ የሚገኝ ሲሆን በ2011 በጀት ዓመት 7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በ2012 በጀት ዓመት መጨረሻ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ሊደርስ ችሏል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት ከሀገር ዉስጥ ኃይል ሽያጭ፣ ከኃይል ኤክስፖርት እና ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ ገቢ በመሰብሰብ ዓመታዊ ገቢውን ወደ 13 ቢሊዮን ለማድረስ ታቅዶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በበጀት ዓመቱ በሁሉም ማከፋፈያ ጣቢያዎች ቆጣሪ በመግጠም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር አዲስ የኃይል ሽያጭ ስምምነት በማዘጋጀት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት እና ተጨማሪ የገቢ ምንጮችን በመለየት የአዋጭነት ጥናት ማካሄድ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ በዕቅዱ ተካቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የታቀደውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ ከማመንጨት እስከ ደንበኛ ድረስ ባለው ሰንሰለት ለኃይል ብክነት መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮችን በመለየት መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

4 + seventeen =