ኢትዮ ቴሌኮም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በ8100 ያሰባሰበውን ከ122 ሚሊዮን ብር በላይ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስረከበ

ኢትዮ ቴሌኮም በ8100 አጭር ቁጥር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሰበሰበውን ገንዘብ ዛሬ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስረክቧል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬህወት ታምሩ በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ እንደገለፁት፣ በ1ኛ ዙር 80 ነጥብ 3 ሚሊዮን እንዲሁም በ2ኛ ዙር 49 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ከደንበኞች ተሰብስቧል።
በአሁኑ የ8100 የ3ኛ ዙር የገቢ ማሰባሰብ ላይ 122 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር መሰብሰቡንና እስካሁን ከተሰበሰበው ገንዘብ እንደሚልቅ አስታውቀዋል።
በሶስቱ ዙሮች ከ252 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን በመጥቀስ ደንበኞች ስላደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በተቋሙና በሰራተኞቹ ስም 111 ሚሊየን ብር የቦንድ ግዢ ማከናወኑንም ወ/ት ፍሬህይወት ተናግረዋል።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ም/ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሔ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከ15 ቢሊየን ብር በላይ በቦንድ ግዢና በልገሳ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
የ8100 የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርም የግድቡ ግንባታ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አጀንዳ እንዲሆን ያደረገና ሁሉም አሻራውን እንዲያሳርፍ እድል የሰጠ ነው ብለውታል።
በመሆኑም ገቢ ማሰባሰቢያው ለቀጣዮቹ 6 ወራት እንዲቀጥል ኢትዮ ቴሌኮምን ጠይቀው ይሁንታ አግኝተዋል።
የተሰባሰበውን ገንዘብ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ አስረክበዋለል።
አቶ አሸብር ባልቻም መላው ህብረተሰብ በ8100 በኩል ሲያደርግ ለቆየው ድጋፍ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስራ አመራር ቦርድ፣ በማኔጅመንቱና በሰራተኞቹ እንዲሁም በፕሮጀክቱ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የተጀመረው ድጋፍ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
0 Comments